በኢትዮጵያ ዋንጫ የሩብ ፍፃሜ የሁለተኛ ቀን ጨዋታ መቻል እና ወላይታ ድቻ ተጋጣሚዎቻቸውን በመርታት ወደ ግማሽ ፍፃሜ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል።
በትላንትናው ዕለት በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ሸገር ከተማ እና ሲዳማ ቡናን ወደ ቀጣዩ ያሳለፈው የኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታ ዛሬም ሁለተኛ ቀን በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ቀጥለው መቻል እና ወላይታ ድቻ ተጋጣሚዎቻቸውን በመርታት ቀጣዩን ዙር መቀላቀላቸውን አረጋግጠዋል። ከቀትር መልስ ቀዝቀዝ ባለው የሀዋሳ አየር ታጅቦ የተጀመረው የመቻል እና ኢትዮጵያ መድን መርሐግብር ቀዳሚው ጨዋታ ነበር። በመጀመሪያው አጋማሽ ተመጣጣኝ እና በተመሳሳይ የሚደረጉ ፈጣን ሽግግሮችን በሁለቱም ቡድኖች በኩል ያየንበት ሲሆን 17ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት ተፈራ ከማዕዘን አሻምቶ መሐመድ አበራ በግንባር ገጭቶ ያሬድ ካሳዬ የመጨረሻዋን ኳስ ወደ ጎልነት ለውጧት መድንን መሪ አድርጓል።
ከጎሏ በተጨማሪ ሜዳ ላይ ትኩረትን የሚስበው የመቻሎቹ አስቻለው ታመነ እና በረከት ደስታ በተከታታይ ተጎድተው መውጣታቸው በአጋማሹ ልትጠቀስ የምትችለዋ ሌላኛዋ አጋጣሚ ሆናለች። ከዕረፍት መልስ በይበልጥ ጨዋታውን በመቆጣጠር ብልጫውን ያሳዩት መቻሎች 55ኛው ደቂቃ ሽመልስ በቀለ የሰጠውን ኳስ ዓለምብርሀን ይግዛው ወደ ግራ ላዘነበለው አዲሱ ፈራሚ ዮሴፍ ታረቀኝ አቀብሎት በጥሩ አጨራረስ ተጫዋቹ ቡድኑን አቻ አድርጓል። 74ኛው ደቂቃ ደግሞ ዮሴፍ ታረቀኝ ከቀኝ ያስጀመረውን ኳስ ያገኘው አብዱልከሪም ወርቁ ከተከላካዮች ጋር ታግሎ የመቻልን ሁለተኛ ግብ ሲያክል ዮዳሄ ዳዊት በጭማሪ ደቂቃ አቡበከር ኑራ መረብ ላይ ያስቆጠራት ሌላኛዋ ጎል መቻልን 3ለ1 አሸናፊ በማድረግ ተቋጭቷል።
በመቀጠል በበርካታ ደጋፊዎች ደምቆ የተካሄደው የወላይታ ድቻ እና ሀዋሳ ከተማ ጨዋታ በመለያ ምት ውጤት የጦና ንቦቹን ከድል ጋር አገናኝቷል። ከፍ ባለ ግለት ከጅምሩ የቀጠለው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ መጠነኛ የሽግግር ጨዋታን የተከተሉት ወላይታ ድቻዎች 35ኛው ደቂቃ ላይ ቴዎድሮስ ታፈሠ ከማዕዘን ያሻማትን ኳስ ውብሸት ክፍሌ በግንባር ወደ ውስጥ ገጭቶ ካመቻቸ በኋላ ካርሎስ ዳምጠው ከመረብ አዋህዶ ጨዋታው 1ለ0 ሆኗል። ከዕረፍት መልስ በተመለሰው ጨዋታ ሀዋሳዎች ውብሸት ክፍሌ ዓሊ ሱለይማን ላይ በሳጥን ውስጥ በሰራው ጥፋት የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ታፈሠ ሰለሞን በቀላሉ በማስቆጠር መደበኛው የጨዋታ ደቂቃ 1ለ1 ተቋጭቷል። በመጨረሻም ቡድኖቹን ለመለየት በተሰጠው የመለያ ምት ወላይታ ድቻ በግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱ ድንቅ ብቃት ታግዞ 3ለ2 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ቀጣዩን ዙር ተቀላቅሏል።