በአህጉራዊ ጨዋታዎች ምክንያት ተቋርጦ የቆየው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በሰንጠረዡ ተከታትለው የተቀመጡት ፈረሰኞቹ እና ነብሮቹ በሚያደርጉት ተጠባቂ ጨዋታ አሃዱ ይላል!
በሰላሣ ነጥቦች 6ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከሁለተኛው ዙር ጅማሮ በኋላ ድል ማድረግ አልቻሉም፤ ቡድኑ ከውድድሩ አጋማሽ በኋላ ከተካሄዱ ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው ዘጠኝ ነጥቦች አንዱን ብቻ በማሳካቱም ደረጃውን ለማስረከብ ተገዷል። ፈረሰኞቹ ላለፉት አምስት ጨዋታዎች ከድል ጋር ቢራራቁም ሰላሣ ሦስት ነጥቦች በመሰብሰብ ተከታትለው ከተቀመጡ ሦስት ቡድኖች ያላቸው የነጥብ ልዩነት ጠባብ ነው። በሁለት ነጥብ ልቆ ከተቀመጠው ሀዲያ ሆሳዕና በሚያደርጉት የነገው ጨዋታ ድል ማድረግ ከቻሉም ደረጃቸው የሚያሻሽሉበት ዕድል ሰፊ ነው፤ ሆኖም በጨዋታው አሉታዊ ውጤት የሚመዘገብ ከሆነ በቀጠናው ካለው የነጥብ መቀራረብ መነሻነት ደረጃቸው አሳልፈው የሚሰጡበት ዕድልም አለ።
አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ቡድናቸው ዳግም ወደ ውጤት ጎዳና ለመመለስ ከቀድሞ ውጤታማነቱ ጋር የማይገኘው የፊት መስመራቸው ማጠናቀር ቀዳሚው ስራቸው መሆን ይገባዋል። በስድስት ጨዋታዎች አስር ግቦች ካስቆጠረ በኋላ በመጨረሻዎቹ አምስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ያስቆጠረው የማጥቃት ጥምረቱ የቀድሞ ጥንካሬውን ማጣቱም ለውጤት ማጣቱ ዋነኛ ምክንያት ተደርጎ ይወሰዳል።
ሰላሣ ሁለት ነጥቦች በመሰብሰብ ከነገው ተጋጣሚያቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ በሁለት ነጥቦች ልቀው 5ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሀድያ ሆሳዕናዎች ከራቃቸው ድል ጋር ለመታረቅ ይፋለማሉ።
እንደ ተጋጣሚያቸው ሁሉ የሁለተኛው ዙር ዐይን ገላጭ ድል ፍለጋ ለማግኘት ወደ ሜዳ የሚገቡት ነብሮቹ በሁለተኛው መንፈቅ ያስመዘገቡት ውጤት በሦስት ደረጃዎች እንዲያሽቆለቁሉ ምክንያት ሆኗል። ነብሮቹ ሁለት ነጥብ ብቻ ከጣሉባቸው ስምንት አስደናቂ የጨዋታ ሳምንታት በኋላ በውጤት ረገድ ተቀዛቅዘዋል፤ ከተጠቀሱት ተከታታይ ድሎች በኋላ በተከናወኑ ስምንት ጨዋታዎች ሦስት ሽንፈት፣ ሦስት የአቻ እና አንድ ድል ማስመዝገባቸውም የዚህ ማሳያ ነው።
ቡድኑ ላይ በተለይም በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች የታየው ስልነት የጎደለው የማጥቃት አጨዋወትም ለተመዘገበው ውጤት እንደ ምክንያትነት መጥቀስ ይቻላል። በባህር ዳር ከተማ ሽንፈት ከገጠማቸው ጨዋታ በኋላ በቡድናቸው በተለይም ከወገብ በላይ ባሉ ተሰላፊዎች ከፍተኛ የድካም ስሜት እንደነበር በማንሳት በመጨረሻዎቹ ሳምንታት አጥጋቢ የፊት መስመር ጥንካሬ እንዳልነበራቸው የገለፁት አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ በነገው ጨዋታ የማጥቃት አጨዋወቱን ጥንካሬ ማጎልበት ቀዳሚ ስራቸው መሆን ይገባዋል። በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ያስቆጠረው የማጥቃት ጥምረቱ በነገው ዕለት የሚኖረው አፈፃፀምም የቡድኑ ውጤት የመወሰን አቅም አለው።
በፈረሰኞቹ በኩል ወደ ሀዋሳ ከተጓዘው ስብስባቸው ሻይዱ ሙስጠፋ እና አብዱልሀዚዝ ቶፊቅ በጉዳት ያልተጓዙ ሲሆን የተቀሩት የቡድኑ አባላት ለነገው ጨዋታ ሀዋሳ መድረሳቸው ታውቋል። በሀድያ በኩል የረጅም ጊዜ ጉዳት ያጋጠማቸው መለሰ ሚሻሞ፣ ጫላ ተሺታ እና በረከት ወንድሙ አሁንም ወደ ልምምድ ያልተመለሱ ሲሆን በኢትዮጵያ ዋንጫ ጥርሱ የወለቀው አንበሉ ሄኖክ አርፊጮ በነገው ጨዋታ የማይኖር መሆኑ ሲታወቅ የቀሩት የቡድኑ ተጫዋቾች ለነገው ጨዋታ ዝግጁ መሆናቸውን አውቀናል።
ቡድኖቹ እስካሁን አስራ አንድ ጊዜ ተገናኝተዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ አራት፤ ሀዲያ ሆሳዕና ሦስት ድሎችን አሳክተው አራት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። በጨዋታዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊስ አስር ሀዲያ ሆሳዕና ደግሞ አምስት ግቦች አስቆጥረዋል።