በወራጅ ቀጠናው አፋፍ እና መውጫ በር ላይ የሚገኙ በሁለት ነጥቦች የሚበላለጡ ክለቦችን የሚያገናኘው ጨዋታ የዕለቱ ሁለተኛ መርሐግብር ነው።
በሀያ ነጥቦች 16ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት አዳማ ከተማዎች በ20ኛው ሳምንት ኤሌክትሪክ ላይ የተቀዳጁትን ድል ደግመው ከረዥም ጊዜያት በኋላ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት በሁለት ነጥቦች ልቆ ከተቀመጠው ድሬዳዋ ከተማ ጋር ይፋለማሉ።
አዳማ ከተማዎች ከብዙዎች ግምት ውጭ በከተማቸው ደካማ የሚባል ውጤት ማስመዝገብ ቢችሉም ከሁለተኛው ዙር ጅማሮ በኋላ በመጠኑም ቢሆን ቀና ብለዋል። ማግኘት ከሚገባቸው አስራ ስምንት ነጥቦች አንዱን ብቻ በማሳካት ደካማ ውጤት ካስመዘገቡባቸው ስድስት የጨዋታ ሳምንታት በኋላ ኤሌክትሪክን በማሸነፍ መጠነኛ እፎይታ ያገኙት አዳማዎች ሁለተኛው መንፈቅ ከተጀመረ ወዲህ በተከናወኑ ሦስት ጨዋታዎች አንድ አንድ ድል፣ ሽንፈት እና የአቻ ውጤት በእኩሌታ በማስመዝገብ መጠነኛ መሻሻል አሳይተዋል።
በአምስት ጨዋታዎች አስራ አንድ ግቦች ማስተናገድ የቻለው የመከላከል ክፍላቸው ከመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች በሦስቱ መረቡን አስከብሮ መውጣቱ እንደ አወንታ የሚጠቀስላቸው ነጥብ ቢሆንም የተጠቀሰው ጥንካሬ ማስቀጠል ግን የአሰልጣኝ አብዲ ቡሊ ቀዳሚው ስራ መሆን ይገባዋል።
አዳማዎች በነገው ጨዋታ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት እንደሚጫወት ቡድን ድል ለማድረግ ብርቱ ፍልሚያ እንደሚያደርጉ የሚጠበቅ ቢሆንም ወደ ወራጅ ቀጠናው የመግባት ስጋት ከተደቀነበት ድሬዳዋ ከተማ የሚገጥማቸው ፈተና ግን ከባድ መሆኑ አይቀሬ ነው።
በሀያ ሁለት ነጥቦች 14ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ድሬዳዋ ከተማዎች ዘለግ ባሉ ሳምንታት ያስመዘገቧቸው ደካማ ውጤቶች ወደ ስጋት ቀጠናው እንዲገቡ ምክንያት ሆነዋል።
በመቀመጫ ከተማቸው ሲዳማ ቡናን ሦስት ለአንድ ካሸነፉ በኋላ ላለፉት አስራ አንድ ጨዋታዎች ከድል ጋር የተራራቁት ብርቱካናማዎቹ ነገ ሙሉ ነጥብ ማሳካት በእጅጉ አስፈላጊያቸው ነው። ካለበት ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር እያንዳንዱን ጨዋታ በጥንቃቄ የመከወን ግዴታ ያለበት ቡድኑ እንደነገው ዓይነት ከቅርብ ተፎካካሪዎች ጋር የሚደረግ ጨዋታ ላይ ድል ማድረግ ካልቻለ አደጋ ውስጥ መግባቱ አይቀሬ ነው፤ ይህ እንዳይሆንም ዘርፈ ብዙ መሻሻሎች ከቡድኑ ይጠበቃሉ። እርግጥ ነው ቡድኑ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ምክንያቶች የፊት መስመር ስብስቡ ሳስቶ መቅረቡ አማራጮችን ያሳጣው ቢሆንም የማጥቃት አጨዋወቱ በቀዳሚነት መሻሻል የሚገባው ጉዳይ ነው።
ድሬዳዋ ከተማ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ የሚታትር ቡድን ቢሆንም በማጥቃቱ ረገድ ግን የቡድኑ የኳስ ፍሰት የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን በብዛት የመፍጠር እና ግብ የማስቆጠር ችግር ይታይበታል። በመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች ግብ ማስቆጠር ያልቻለው ቡድኑ በተጋጣሚ የግብ ክልል አከባቢ ያለበትን ችግር ቀርፎ መቅረብ ግድ ይለዋል። ብርቱካናማዎቹ የፊት መስመራቸው ለማሻሻል በዝውውር መስኮቱ ሀቢብ ከማል፣ አቡበከር ወንድሙ እና ዮሐንስ ደረጄን ማስፈረምም ችለዋል።
በአዳማ ከተማ በኩል የግብ ጠባቂው ዳግም ተፈራ መሰለፍ አጠራጣሪ ከመሆኑ ውጪ ሁሉም የቡድኑ አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።በድሬዳዋ ከተማ በኩል ከመሐመድኑር ናስር ውጭ በጉዳትም ይሁን በቅጣት ጨዋታው የሚያመልጠው ተጫዋች የለም፤ በዝውውር መስኮቱ አጋማሽ ቡድኑን የተቀላቀሉ ተጫዋቾችም ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።
ረዘም ያለ የግንኙነት ታሪክ ያላቸው ሁለቱ ቡድኖች በአጠቃላይ በሊጉ 25 ጊዜ ሲገናኙ አዳማ ከተማዎች 12 ጊዜ ባለድል በመሆን የበላይ ሲሆኑ ድሬዳዋ ከተማዎች ደግሞ በ6 ይከተላሉ የተቀሩት 7 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተቋጩ ነበሩ። በጨዋታዎቹ አዳማዎች 29 ሲያስቆጥሩ ድሬዎች በአንጻሩ 21 ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል።