በአዲስ መልክ እድሳት በተደረገለት የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም የተካሄደው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የሀድያ ሆሳዕና የሀዋሳ ከተማ የሊጉ ቆይታ የመክፈቻ ጨዋታ ያለ ምንም ጎል ተጠናቋል።
ለዋልያዎቹ የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታ ሊጉ ከመቋረጡ አስቀድሞ በ22ኛው ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ያለ ጎል ከተለያዩበት ጨዋታ በኋላ ሲመለሱ ቶሎሳ ንጉሴ ፣ አብርሀም ጌታቸው ፣ አብዱልሀዚዝ ቶፊቅ ፣ ተገኑ ተሾመን እና አማኑኤል አረቦን አሳርፈው በምትካቸው ጳውሎስ ከንቲባ፣ ሀብታሙ ጉልላት፣ የዓብስራ ጎሳዬ፣ ዳግማዊ አርአያ፣ ቢንያም ፍቅሬ እና ፀጋ ከድርን ይዘው ወደ ሜዳ ሲገቡ ሀድያ ሆሳዕናዎችም በበኩላቸው በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረባቸው ጎል በባህር ዳር ከተማ ከደረሰባቸው ሽንፈት በኋላ ወደ ሜዳ ሲመለሱ ሄኖክ አርፊጮ እና ከማል ሀጂን በቃለዓብ ውብሸት እና አስጨናቂ ሉቃስ ብቻ ቀይረው ለጨዋታው ቀርበዋል።
ፌደራል ዳኛ ሄኖክ አበበ ባስጀመሩት የሀዋሳ ሜዳ የመክፈቻ ጨዋታ ፈረሰኞቹ በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ ወደ ፊት በመሄድ ከሀድያዎች በተሻለ ሆነው በታዮበት የመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ውስጥ በ10ኛው ደቂቃ ከሳጥን ውጭ ከጎሉ ፊት ለፊት የተገኘውን ቅጣት ምት ቢንያም ፍቅሬ በቀጥታ መቶ ግብ ጠባቂው ሚካኤል ሳማኪ ያዳነበት እንዲሁም ከሁለት ደቂቃ በኋላ በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ሄኖክ ዮሐንስ በጥሩ መንገድ የሰነጠቀለትን ራሱ ቢንያም በቀላሉ ወደ ጎልነት ቀየረው ሲባል በግቡ ቋሚ በኩል ወደ ውጭ የወጣበት ኳስ ለቅዱስ ጊዮርጊሶች የሚያስቆጩ አጋጣሚዎች ነበሩ።
በተቆራረጡ ኳሶች ወደ ማጥቃት ሽግግሩ የሚገቡት ሀድያ ሆሳዕናዎች በ18ኛው ደቂቃ እዮብ አለማየሁ ከራሳቸው የሜዳ ክፍል በቀኝ መስመር በግል ጥረቱ ኳሱን እየነዳ በመግባት ከተመስገን ጋር ተቀባብሎ ሳጥን ውስጥ የገባው ኢዮብ ኳሱን በግብጠባቂው ተመስገን ላይ ቺብ አድርጎ በግቡ አናት የወጣበት ለነብሮቹ ወደ ጨዋታው እንዲገቡ ያነቃቃች ሙከራ ነበር።
ጨዋታው በዚህ ፍጥነት ቀጥሎ ተደጋጋሚ የጎል ሙከራዎች በሁለቱም በኩል ያስመለክተናል ተብሎ ቢጠበቅም በቀሩት ሃያ አምስት ደቂቃዎች ይህ ነው ተብሎ የሚጠቀስ የጠራ የጎል ሙከራ ሳያስመለክተን በፈረሰኞቹ በኩል ከራሳቸው የሜዳ ክፍል በጥሩ የኳስ ቅብብሎች የመውጣትን ሂደት በነብሮቹ በኩል የፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ አስመልክቶን አጋማሹ ተጠናቋል።
ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ ነብሮቹ በደቂቃዎች ልዮነት ወደ ግራ መስመር አድልተው ባደረጉት ጥቃታ እዮብ አለማየሁ ጣጣውን ጨርሶ ሳጥን ውስጥ ያቀበለው ኳስ ብሩክ በየነ ግልፅ የማግባት አጋጣሚ ሳይጠቀምበት የቀረው እና ከሰከንዶች በኋላ በድጋሚ ሦስቱ የፊት አጥቂዎች በአንድ ሁለት ቅብብል የፈጠሩትን ሰመረ ወደ ውስጥ ገብቶ ያቀበለውን ብሩክ ማርቆስ ያመከነው ነብሮቹ ከዕረፍት መልስ ተለውጠው የመጡበት ማሳያዎች ነበሩ።
በሁለቱም በኩል እንደ ቡድን ክፍት ሜዳዎችን ፈልጎ የጎል ዕድሎችን ከመፍጠር ይልቅ ግላዊነት የበዛበት እንቅስቃሴን ለማሳየት የሚያደርጉት ጥረት ስኬታማ አለመሆኑ ተከትሎ ዘለግ ላሉ ደቂቃዎች ሙከራዎችን እንዳንመለከት አድርጎት ጨዋታውን ወደ አሰልቺነት ቀይሮታል። የጨዋታው የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ጎሎችን ለማስቆጠር በተለይ ፈረሰኞቹ ከቆሙ ኳሶች ጫና ለመፍጠር ቢያስቡም ጨዋታው 0-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።