ሪፖርት | የምስራቁ ክለብ ከ11 ጨዋታዎች በኋላ ከድል ጋር ታርቋል

ሪፖርት | የምስራቁ ክለብ ከ11 ጨዋታዎች በኋላ ከድል ጋር ታርቋል

አዳማ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማን ያገናኘው ጨዋታ በብርቱካናማዎቹ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።



ከሀገራት ጨዋታ መልስ ውድድሩን በሐዋሳ ከተማ አድርጎ የጀመረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ቀን ሁለተኛ ጨዋታ በነበረው እና አዳማ ከተማን ከድሬዳዋ ከተማ 12:00 ሲል ያገናኘው ጨዋታ ነበር።

ጨዋታውም በሁለቱም ቡድኖች በኩል መጠነኛ የሆነ የኳስ እንቅስቃሴ የተደረገበት ነበር። በመጀመሪያው አጋማሽ ብልጫ ወስደው ሲጫወቱ የነበሩት ድሬዳዋ ከተማዎች በቁጥር በዛ ብለው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ የቻሉ ሲሆን የልፋታቸውን ውጤት ለማየት 20 ደቂቃ ያክል በቂ ነበር።

20 ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩት ድሬዳዋ ከተማዎች አስራት ቱንጆ ለቻርለስ ሙሰጌ አሾልኮ ያቀበለውን ኳስ ጥሩ በሚባል አጨራረስ ቻርለስ ወደ ግብነት ቀይሮ የምስራቁን ክለብ መሪ ማድረግ ችሏል።

ከግቡ መቆጠር በኋላ ሁለቱም ቡድኖች ጥሩ እንቅስቃሴዎችን ቢያደርጉም ተጨማሪ ሙከራ ሳያደርጉ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ከበፊቱ ተሻሽለው የቀረቡት ድሬዳዋ ከተማዎች 63 ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር ጀሚል ያዕቆብ በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ሳጥን ገብቶ ያቀበለውን ኳስ ተቀይሮ የገባው ዮሐንስ ደረጄ ወደ ግብነት ቀይሮ ለቡድኑ ሁለተኛውን ግብ ማስቆጠር ችሏል።

አሁንም ያስቆጠሩት አልበቃ ያላቸው ሚመስሉት ድሬዳዋ ከተማዎች አጥብቀው በማጥቃት ሶስተኛ ግባቸውን ማስቆጠር ችለዋል። 76ተኛው ደቂቃ ላይ አብዱልሰላም የሱፍ ለቻርለስ ሙሰጌ አቀብሎት የገባውን ኳስ መልሶ ራሱ ተቀብሎ በድንቅ አጨራረስ ወደ ግብነት ቀይሮ የግቡን ልዩነት ማስፋት ችሏል።

78ኛው ደቂቃ ላይ የማዕዘን ምት ያገኙት አዳማ ከተማዎች የጎል ልዩነቱን ማጥበብ የቻሉበትን ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ አድናን ረሻድ በግንባሩ ገጭቶ አከራካሪ የነበረውን ኳስ ማስቆጠር ችሏል። ይህንንም ተከትሎ የግብ ልዩነቱን ወደ ሁለት ማጥበብ ችሏል።


አዳማ ከተማዎች ከግቡ መቆጠር በኋላ ጫና ፈጥረው መጫወት ቢችሉም ጠንካራውን የድሬዳዋ ተከላካዮች አጥር መስበር ተስኗቸው ጨዋታው በድሬዳዋ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።