የ23ኛው ሳምንት ሁለተኛ የጨዋታ ቀን ቢጫዎቹ እና ዐፄዎቹ በሚያደርጉት የረፋድ ጨዋታ ይጀመራል።
በውድድር ዓመቱ ባስመዘገቡት ደካማ ውጤት ለሀያ ሦስት ሳምንታት በሰንጠረዡ ግርጌ ለመቀመጥ የተገደዱት ወልዋሎዎች ዘጠኝ ነጥቦች ሰብስበዋል።
ቢጫዎች አሁንም ከግርጌው መላቀቅ ባይችሉም ብያንስ ከተከታታይ ሽንፈቶች መራቃቸው በአወንታ የሚነሳላቸው ነጥብ ነው፤ አንድ ነጥብ ብቻ ካስመዘገቡባቸው የመጀመርያዎቹ አስራ ሁለት መርሐ-ግብሮች በኋላ ተከታታይ ሽንፈት ያልቀመሱት ወልዋሎዎች በመጨረሻዎቹ ስምንት ጨዋታዎች በአንፃራዊነት የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል። በሊጉ ለመትረፍ ትልቅ ስራ መስራት የሚጠበቅበት ቡድኑ የነጥብ ልዩነቱ አጥብቦ በወራጅ ቀጠናው ካሉ ክለቦች በቅርበት ለመፎካከር ግን በቀሩት መርሐ-ግብሮች እንደ ፍፃሜ መፋለም ብቸኛው አማራጩ ነው።
ክለቡ ስድስት አዳዲስ ተጫዋቾች በማስፈረም በዝውውር መስኮቱ ንቁ ተሳትፎ ማድረጉን ተከትሎ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም በነገው ዕለት የሚኖራቸው አቀራረብ እና የተጫዋቾች ምርጫ ለመገመት የሚያዳግት ቢሆንም በቋሚ አሰላለፉ አዲስ ጥምረት መኖሩ አይቀሪ ነው። ሁለት ሽንፈት እና ሁለት የአቻ ውጤቶች ባስመዘገበባቸው ያለፉት አራት ጨዋታዎች ላይ በማጥቃት አጨዋወቱ ላይ ክፍተቶች የተስተዋለበት ቡድኑ በተጠቀሱት መርሐ-ግብሮች የተጋጣሚን የተከላካይ መስመር ሰብሮ በርከት ያሉ ንፁህ የግብ ዕድሎች መፍጠር ተስኖት ነበር፤ በነገው ዕለትም ባለፉት አራት ጨዋታዎች ላይ አንድ ግብ ያስቆጠረው የፊት መስመራቸው ማሻሻል ቀዳሚ ስራቸው መሆን ይገባዋል።
በ22ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ላይ መቻልን ከጨዋታ ብልጫ ጋር አሸንፈው ነጥባቸው ሀያ ሰባት ያደረሱት ፋሲል ከነማቸው ከሰንጠረዡ አጋማሽ ለመሻገር ከነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማግኘት ግድ ይላቸዋል።
ሊጉ በሀገራዊ ጨዋታዎች ከመቋረጡ በፊት በተካሄደ የመጨረሻ ጨዋታ ያገኙትን የአሸናፊነት መንገድ የማስቀጠል ዓላማን ሰንቀው ወደ ነገው ጨዋታ የሚቀርቡት ዐፄዎቹ መቻልን ባሸነፉበት እና በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ከሁለት ግብ በላይ ባስቆጠሩበት መርሐ-ግብር ከወትሮ የተለየ ጥሩ ተነሳሽነት ነበራቸው። በጨዋታው የተሻለ ብልጫ የነበረው ቡድኑ በተለይም በግብ ማስቆጠሩ ረገድ የነበረው ችግር መቅረፉ ከወሳኙ ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ይዞ እንዲወጣ አስችሎታል።
ከዚህ ቀደም ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ከመድረስ ባለፈ የግብ ዕድሎችን የመፍጠር ክፍተት የነበረበት የአሰልጣኝ ውበቱ አባተው ቡድን በማጥቃቱ ረገድ ለነገው ጨዋታ የሚተርፍ ዓይነት መሻሻልን አሳይቷል።
መድን እና ድሬዳዋ ከተማ ላይ ከተመዘገቡ ተከታታይ ሁለት ድሎች በኋላ በተከናወኑ ሦስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው ዘጠኝ ነጥቦች
አንዱን ብቻ ካሳኩ በኋላ ዳግም ወደ ድል የተመለሱት ዐፄዎቹ በቀጣይ የወጥነት ችግራቸው የመቅረፍ ስራ ይጠብቃቸዋል። ይህ እንዲሆንም በመቻሉ ጨዋታ የነበረው የድል ረሀብ እና የተሻሻለ የማጥቃት አጨዋወት እንዲሁም ውጤታማው የቆመ ኳስ አጠቃቀም ማስቀጠል ይኖርባቸዋል።
ወልዋሎዎች በመጨረሻው የሊግ ጨዋታ በቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣው ዩጋንዳዊው ሙሳ ራማታህ በቅጣት፤ በረከት አማረ እና ኤፍሬም ኃይለማርያም ደግሞ በጉዳት ምክንያት በነገው ጨዋታ አያሰልፉም። በፋሲል ከነማ በኩል የቡድን ዜና ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
ቡድኖቹ የተሰረዘው እና በፋሲል ከነማ 1ለ0 አሸናፊነት የተጠናቀቀው የ2012 ውድድር ዓመት ጨዋታ ሳይጨምር በሊጉ አምስት ጊዜ ተገናኝተው ፋሲል ከነማ ሦስት ጊዜ ሲያሸንፍ በሁለቱ አቻ ተለያይተው ወልዋሎ ምንም አላሸነፈም።