ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ወላይታ ድቻ  ከ መቐለ 70 እንደርታ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ወላይታ ድቻ  ከ መቐለ 70 እንደርታ

የመጨረሻ የሊግ ጨዋታቸውን በድል ያጠናቀቁት የጦና ንቦቹ እና ምዓም አናብስት የሚፋለሙበት ጨዋታ 9:00 ይጀመራል።


በሁለተኛው ዙር በተካሄዱ ሦስት ጨዋታዎች ሙሉ ነጥብ ማግኘት የቻሉት የጦና ንቦቹ ሰላሣ ሦስት ነጥቦች በመሰብሰብ ከመሪዎቹ ጎራ ተቀላቅለዋል።

ሦስት ተከታታይ ድሎች በማስመዝገብ ከዋንጫ ተፎካካሪ ቡድኖች ጎራ የተቀላቀሉት የጦና ንቦቹ በአስደናቂው የአምስት ጨዋታዎች ጉዞ  ያሳዩት ብቃት ብዙ የሚያስወድሳቸው ነበር። ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው አስራ አምስት ነጥብ አስራ ሦስቱን ማሳካት የቻለው ቡድኑ ከውጤቱ ባሻገር ዘርፈ ብዙ መሻሻሎች አሳይቷል።
በተለይም በሁለት ጨዋታዎች አራት ግቦች አስተናግዶ የነበረው የቡድኑ የተከላካይ መስመር ባለፉት አምስት ጨዋታዎች በአራቱ መረቡን በማስከበር ጉልህ መሻሻል አሳይቷል። እርግጥ ቡድኑ በጥሩ ወቅታዊ ብቃት መገኘቱ የማያጠያይቅ ጉዳይ ቢሆንም በመጨረሻዎቹ አምስት ጨዋታዎች በጨዋታ ከአንድ ግብ በላይ ማስቆጠር ያልቻለው የማጥቃት አጨዋወቱ ግን እውነተኛ የዋንጫ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቀጠል በግብ ማስቆጠሩ ረገድ ይበልጥ መሻሻል ያስፈልገዋል።

በመጨረሻው ሳምንት አርባምንጭ ከተማ ላይ ወሳኝ ድል አስመዝግበው ነጥባቸው ሀያ አምስት ያደረሱት መቐለ 70 እንደርታዎች ከአደጋው ቀጠና  ለመራቅ ድል ማድረግ አስፈላጊያቸው ነው።

ከተከታታይ አራት ድል አልባ ጨዋታዎች በኋላ አዞዎቹን ረተው መጠነኛ እፎይታ ያገኙት ምዓም አናብስት በአራት የጨዋታ ሳምንታት አንድ ነጥብ ብቻ ካሳኩባቸው መርሐ-ግብሮች መልስ ያገኙት ወሳኝ ድል ለማስቀጠል በጥሩ ወቅታዊ አቋም የሚገኙትን የጦና ንቦች ለመፋለም ነገን ይጠባበቃሉ። መቐለ ከተከታታይ ሦስት ሽንፈቶች መልስ ድል ማድረጉ በውጤት ረገድ ተጠቃሚ ያደረገው ቢሆንም በጨዋታው ያሳየው ብቃት ግን መሻሻል የሚገባው ነው። በነገው ጨዋታ ቀላል የማይባል ፈተና የሚጠብቀው ቡድኑ በነገው ዕለት ሦስት ተከታታይ ድሎች ያስመዘገበ እና በአምስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ያስተናገደ ቡድን እንደ መግጠሙ በብዙ ረገድ ተሻሻሽሎ መቅረብ ግድ ይለዋል፤ በተለይም የመከላከል አደረጃጀቱ።

በ21ኛ ሳምንት በተደረገው እና በሀዋሳ ከተማ አምስት ግቦች አስተናግዶ በተሸነፈበት ጨዋታ ቡድኑ የኋላ መስመሩ የመዋቅር ክፍተቶችን ሲያስመለክት ነበር። ቡድኑ ከሊጉ ሦስት ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ክለቦች አንዱ ከሆነው አርባምንጭ ከተማ ጋር ባካሄደው ጨዋታ የተሻሻለ የመከላከል አደረጃጀት ገንብቶ መረቡን አስከብሮ መውጣት ቢችልም በቀጣይ ግን ዘጠኝ ግቦች ባስተናገደባቸው ከ18ኛው እስከ 21ኛው ሳምንት በተካሄዱ አራት ጨዋታዎች ላይ የተስተዋሉ የመከላከል ስህተቶች በዘላቂነት መፍታት ይጠበቅበታል። ቡድኑ በዝውውር መስኮቱ መክብብ ደገፉ፣ ኢማኑኤል ላርያ እና ንግኖዋ ሀፕሞ ማን ይክረ ዳንግሞ አስፈርሞ በርከት ያሉ ተጫዋቾች ከጉዳት መልስ ማግኘቱ ነገሮችን አስተካክሎ እንዲቀርብ ሊረዳው ይችላል፤ ነገም በአምስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ላስተናገደው የወላይታ ድቻ ጠጣር የመከላከል አደረጃጀት የሚመጥን የማጥቃት አቀራረብ ማበጀት ይኖርበታል።

በወላይታ ድቻ በኩል ተከላካዩ መልካሙ ቦጋለ ከጉዳቱ አገግሞ ወደ ልምምድ መመለሱ ቢሰማም ለነገው ጨዋታ የመድረሱ ነገር አልተወሰነም። ሌሎቹ የቡድኑ አባላት ግን ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው። በመቐለ 70 እንደርታ በኩል ተመስገን በጅሮንድ፣ ሔኖክ አንጃው እና ያሬድ ብርሃኑ በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ ናቸው።

ቡድኖቹ በሊጉ ለአምስት ጊዜያት የተገናኙ ሲሆን መቐለ 70 እንደርታ 3 ስያሸንፍ ወላይታ ድቻ  2 ጨዋታዎች አሸንፏል። በጨዋታዎቹ ምዓም አናብስት 4 ግቦች ሲያስቆጥሩ የጦና ንቦቹ  ሁለት ግቦች አስቆጥረዋል።