በሀያ ነጥቦች 15ኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ የወራጅ ቀጠናው መውጫ በር እያማተሩ የሚገኙት ሀዋሳ ከተማዎች መሪው ኢትዮጵያ መድንን በመግጠም ውድድራቸው ይጀምራሉ።
ከፍተኛ የወጥነት ችግር ኖሮባቸው የመጀመሪያውን ዙር ያገባደዱት ሀይቆቹ አሰልጣኝ ሙልጌታ ምሕረትን ከሾሙ በኋላ በጥሩ ተነሳሽነት ይገኛሉ። በሁለተኛው ዙር ከተካሄዱት ሦስት ጨዋታዎች አንድ ድል እና ሁለት የአቻ ውጤቶች ያስመዘገበው ቡድኑ ከውጤቱ ባሻገር በእንቅስቃሴ ረገድ ጥሩ መሻሻሎች አሳይቷል። ቡድኑ ከዋንጫ ተፎካካሪዎቹ ሀድያ ሆሳዕና እና ኢትዮጵያ ቡና ነጥብ በተጋራባቸው እንዲሁም ከአስራ አራት ጨዋታዎች ጥበቃ በኋላ በጨዋታ ከአንድ ግብ በላይ አስቆጥሮ በጎሎች ተንበሽብሾ ድል ያደረገበት የመቐለው ጨዋታ ያሳየው ብቃትም ለቡድኑ መሻሻል ሁነኛ ማሳያዎች ናቸው።
ሀዋሳ ከተማዎች ጠንካራ ቡድኖች በገጠሙባቸው ሁለት ጨዋታዎች መረባቸውን ሳያስደፍሩ መውጣታቸው ወደነገው ጨዋታ በተሻለ የራስ መተማመን እንዲቀርቡ የሚያስችላቸው ቢሆንም በማጥቃቱ ረገድ ግን አሁንም ከባድ ስራ እንደሚቀራቸው እሙን ነው። ቡድኑ በነገው ዕለት የሊጉ ጠንካራው የመከላከል ጥምረት እንደመግጠሙ የማጥቃት አጨዋወቱን ጥራት ከፍ አድርጎ መቅረብ ግድ ይለዋል። አሰልጣኝ ሙልጌታ ምሕረት በነገው ጨዋታ በመልሶ ማጥቃቶች እና ሽግግሮች በሚገኙ ዕድሎች ግብ ለማስቆጠር ያለመ የጨዋታ ዕቅድ ይዞ ይቀርባል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ከተጋጣሚው ክብደት አንፃር መከላከል አደረጃጀቱ ከፍ ያለ ትኩረት ሰጥቶ መግባት ከጨዋታው የሚፈልገው እንዲያገኝ ሊረዳው ይችላሉ።
የማጥቃት አጨዋወቱ ዒላማ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው ፈጣኑ ዓሊ ሱሌይማን ከመድን ተከላካዮች የሚያደርገው ፍልምያም ጨዋታው ተጠባቂ የሚያደርገው ሌላ ነጥብ ነው።
አርባ አንድ ነጥቦች የሰብሰቡት ኢትዮጵያ መድኖች ከተከታዮቻቸው በስምንት ነጥቦች ልዩነት መሪነቱ ላይ ተሰይመዋል።
መድን በሊጉ ጥቂት ሽንፈት የቀመሰ ቡድን ነው። በሁለተኛው ዙር ጅማሮ በወላይታ ድቻ ከደረሰበት ሽንፈት አገግሞ ተከታታይ ሁለት ድሎች በማስመዝገብም ኮስታራ የዋንጫ ተፎካካሪ መሆኑ አስመስክሯል። ኢትዮጵያ መድን ከዚህ ጨዋታ በፊት በስነ ልቦና ጥንካሬ ከፍታ ላይ እንዲገኝ የሚያደርጉት ብዙ ነገሮች አሉ። ሊጉን በስምንት ነጥቦች ልዩነት መምራት መጀመሩ፤ የቡድኑ ዋነኛ ጥንካሬ የሆነው የመከላከል ብርታት ይዞ መቀጠሉ እንዲሁም ከባድ የነበረውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጨዋታ ማሸነፉ በዚህ ረገድ የሚነሱ ነጥቦች ናቸው።
መድን ውጤት ከማሳካት ባለፈ ከኳስ ውጪ በቀላሉ ክፍተት የማይሰጥ አደረጃጀትን መከተሉ እንዲሁም ግቦች ከተለያዩ አቅጣጫዎች እያገኘ መቀጠሉ አስፈሪነቱን አላብሶታል። ከተጋጣሚው ባህሪ አንፃር በነገው ጨዋታ የተሻለ ኳስ ቁጥጥር ብልጫ ይኖረዋል ተብሎ የሚጠበቀው ቡድኑ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥንቃቄን ሊመርጥ በሚችለው ተጋጣሚው የኋላ ክፍል ክፍተቶችን ለማግኘት መፈተኑ የሚቀር ባይመስልም ባለፉት አራት ጨዋታዎች ስድስት ግቦች ያስቆጠረው የቡድኑ ማጥቃት አጨዋወት እንዲሁም በግለ ሰብ ደረጃ በእግርኳስ ሂወቱ ምርጥ ጊዜ ላይ የሚገኘው ወጣቱ መሐመድ አበራ ለተጋጣሚው ፈተና መሆናቸው አይቀሪ ነው።
በሀዋሳ ከተማ በኩል በረከት ሳሙኤል በጉዳት እስራኤል እሸቱ ደግሞ በአምስት ቢጫ ካርድ ምክንያት በቅጣት ከነገው ጨዋታ ውጪ ናቸው።
በኢትዮጵያ መድን በኩል ሚልዮን ሰለሞን አሁንም ጉዳት ላይ ሲገኝ አብዲሳ ጀማል እና ረመዳን የሱፍ ወደ ልምምድ የተመለሱ ሲሆን አብዲሳ ጀማል የነገው የጨዋታ ዕለት ስብስብ ውስጥ እንደሚካተት ይጠበቃል።
ሁለቱ ክለቦች በአጠቃላይ 30 ጊዜ ተገናኝተው ሀዋሳ 13 በማሸነፍ ከፍተኛ የበላይነት ሲኖረው መድን 5 አሸንፏል። 12 ጨዋታዎችን በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ናቸው። ሀዋሳ ከተማ 38 ፣ መድን 30 አስቆጥረዋል።