ፋሲል ከነማ በጌታነህ ከበደ እና ሸምሰዲን መሐመድ ጎሎች ከመመራት ተነስቶ ወልዋሎ ዓ.ዩን 2ለ1 አሸንፏል።
ሊጉ በዋልያዎቹ ጨዋታ ከመቋረጡ በፊት ወልዋሎ አዲግራት ዩ በወላይታ ድቻ አንድ ለምንም ከተረቱበት ጨዋታ ላይ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ባደረጉት የሦስት ተጫዋቾችን ለውጥ ግብ ጠባቂው በረከት አማረ፣ ዳዊት ገብሩን እና ሳምሶን ጥላሁን ወጥተው ግብ ጠባቂ ኦሎሩንለኪ ኦሉዋሴጎን፣ ሳሙኤል ዮሐንስን እና ሰለሞን ገመቹን ገብተዋል። ፋሲል ከነማዎች በአንፃሩ መቻልን አራት ጎል አስቆጥረው ድል ካደረጉበት አሰላለፍ አራት ተጫዋቾችን ለውጥ አድርገው ብሩክ አማኑኤልን፣ አቤል እንዳለን፣ አሚር ሙደሲርን እና ማርቲን ኬዛን በዮናታን ፍስሃን፣ በጃቢር ሙሉን፣ በሀብታሙ ተከስተ እና አንዋር ሙራድን ተክተው ገብተዋል።
የዕለቱን የረፋድ ቀዳሚ ጨዋታ ፌደራል ዳኛ መስፍን ባስጀመረው ጨዋታ ገና በአርባኛው ሰከንድ ነበር የጨዋታው የመጀመርያ ሙከራ የተደረገው። ወልዋሎዎች ሳሙኤል ዮሐንስ ከመሐል ሜዳ ያሻገረውን ዳዋ ሆጤሳ ከተከላካዮች ሲታገል ቡልሻ ሹራ ኳሷን ሳጥን ውስጥ አግኝቶ ወደ ጎል የመታውን ግብጠባቂውን ፋሲል ገብረሚካኤል እንደምንም አድኖታል።
ከዚህ ሙከራ በኋላ የጨዋታው ፍሰት እየተቆራረጠ ቀዝቀዝ ያለ መልክ ይዞ ሲቀጥል ቡድኖቹ በራሳቸው የሜዳ ክፍል ከሚያደርጉት የተሳካ ቅብብሎች ውጭ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ዘልቀው በመግባት አደጋ ለመፍጠር ሲቸገሩ አስተውለናል። ሆኖም በጨዋታው 19ኛው ደቂቃ በዐፄዎቹ በኩል አጥቂዎች ጥሩ አጋጣሚ አግኝተው ለኳሱ ዝግጁ ሳይሆኑ በቀላሉ ኳሱን መቆጣጠር ተስኗቸው ያመለጣቸው እንዲሁም በ28ኛው ደቂቃ ላይ ቢጫ ለባሾቹ በአንድ ሁለት ቅብብል ሳጥን ውስጥ ዳዋ ሆቴሳ አግኝቶ በፋሲል ተከላካዮች ተደርቦ የወጣው ኳስ በጨዋታው እስከ ሠላሳ አምስተኛው ደቂቃ ድረስ የተፈጠሩ ዒላማውን ያልጠበቀ ሙከራዎች ነበሩ። በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ በሁለቱም በኩል ተመጣጣኝ የነበረ ቢሆንም አብዛኛውን የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ስል ያልነበረ በመሆኑ እና የተከላካይ ክፍላቸው ንቁ መሆናቸውን ተከትሎ በጎል ሙከራ ረገድ የተለየ ነገር ሳያስመለክቱን የመጀመርያው አጋማሽ ሊገባደድ ችሏል።
እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሳይሆን ጎል ያስመለከተን ሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታውን እንቅስቃሴ ቀጥሎ የመጀመርያ ጎል በ59ኛው ደቂቃ ላይ አስመልክቶናል። ወልዋሎዎች ከራሳቸው የሜዳ ክፍል ኳሱን አደራጅተው በመውጣት ናሆም ከቀኝ መስመር የጣለውን ከሰለሞን በጥሩ መንገድ የተቀበለው ቡልቻ ሹራ ከጎሉ ፊት ለፊት ሳጥን መስመር ላይ ቦታ አይቶ በመምታት ቡድኑን መሪ አድርጓል።
ከጎሉ መቆጠር በኋላ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ዐፄዎች የማጥቃት አቅማቸውን ለማሳደግ ፈጣን የሁለት ተጫዋቾችን ቅያሪ በማድረግ ተጭነው መጫወታቸውን ቀጥለው ተቀይሮ የገባው አማኑኤል ገብረሚካኤል ከግራ መስመር ተከላካይ ቀንሶ ወደ ውስጥ በመግባት በጥሩ እይታ ያቀበለውን ጌታነህ ከበደ በጥሩ አጨራረስ ቡድኑን አቻ አድርጓል።
ጨዋታው ወደ አንድ አቻ ውጤት ከተቀየረ በኋላ ምላሽ ለመስጠት የሞከሩት ወልዋሎዎች በ72ኛው ደቂቃ ኪሩቤል ወንድሙ በግራ መስመር ገፍቶ በመግባት ቡልቻ ሹራ ተቀብሎ ደገፍ አድርጎ የመታው እና ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣበት የምታስቆጭ ነበረች። አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ያደረጉት ሌላኛው የተጫዋች ቅያሪ ውጤታማ አድርጓቸው ጨዋታውን ማሸነፍ የቻሉበትን ወሳኝ ጎል በመጨረሻው ደቂቃ አግኝተዋል።
90ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር የተገኘውን ቅጣት ምት ጌታነህ ከበደ ሲያሻግር ተቀይሮ የገባው ሸምሰዲን መሐመድ በግንባሩ በመግጨት ለቡድኑ ማሸነፊያ ሁለተኛውን ጎል አስገኝቷል። ቢጫ ለባሾቹ አስቀድመው መምራት ቢችሉም በኋላም ጨዋታው ከእጃቸው አምልጧቸው ሲሸነፉ በአንፃሩ ፋሲል ከነማዎች በሁለተኛው አጋማሽ ባስቆጠሩት ሁለት ጎሎች ተከታታይ ድላቸውን አሳክተው ጨዋታው ተጠናቋል።