ሪፖርት | የጦና ንቦቹ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከፍ ያሉበትን ድል ተቀዳጅተዋል

ሪፖርት | የጦና ንቦቹ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከፍ ያሉበትን ድል ተቀዳጅተዋል

ወላይታ ድቻ በፍጹም ግርማ ብቸኛ ግብ ለአራተኛ ተከታታይ ጨዋታ 1-0 በማሸነፍ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከፍ ብሏል።

ወላይታ ድቻዎች በ22ኛ ሳምንት በካርሎስ ዳምጠው ብቸኛ ጎል ወልዋሎን ካሸነፉበት ጨዋታ ከተጠቀሙበት አስተላለፍ አዛርያስ አቤል እና ኬኔዲ ከበደን ለውጠው ተስፋዬ መላኩ እና ውብሸት ክፍሌ ተክተው በማስገባት ሲቀርቡ መቐለ 70 እንደርታ በበኩላቸው ዘረሰናይ ብርሀኔ፣ ኪሩቤል ሀይሉ እና ያሬድ ብርሀኑ አሳርፈው ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ፣ ቤንጃሚን ኮቴ እና አሸናፊ ሐፍቱን በማስገባት ጨዋታውን ጀምረዋል።

በርከት ባሉ ደጋፊዎች ታጅቦ የተካሄደውን ጨዋታ ፌደራል ዋና ዳኛ ሙሉቀን ያረጋል አስጀምረውታል። ተመጣጣኝ የሆነ የሜዳ ላይ ፉክክር እያስመለከተን በዘለቀው በዚህ ጨዋታ
መቐለ 70 እንደርታዎች ቦና አሊ እና በቡሩክ ሙልጌታ አማካኝነት የጎል ዕድሎችን መፍጠር ችለው ነበር። በተለይ በ14ኛው ደቂቃ ቦና አሊ ከሳጥን ውጭ በግራ እግሩ የመታው እና ግብጠባቂውን ቢንያም ገነቱን ማለፍ ያልቻለው ኳስ ጥሩ ሙከራቸው ነበር።

ከወትሮው በተወሰነ መልኩ ከሚታወቁበት ፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ተቀዛቅዘው የታዩት የጦና ንቦቹ በ19ኛው ደቂቃ መቐለ 70 እንደርታ ተከላካዮች ዐየር ላይ ያለውን ኳስ በተገቢው መንገድ አለማራቃቸውን ተከትሎ የመስመር አጥቂ ፀጋዬ ብርሀነ ዘሎ በግንባሩ የገጨውን ግብጠባቂው ሶፎንያስ የመለሰበት በተወሰነ መልኩ ደጋፊዎቻቸውን ከዝምታ ያነቃች ሙከራ ነበረች።

በሂደት መነቃቃት የጀመሩት ወላይታ ድቻዎች በ34ኛው ደቂቃ መሪ የሆኑበትን ጎል አስቆጥረዋል። ከተከለላካይ ጀርባ የተላከለትን ያሬድ ደርዛ ሳጥን ውስጥ በመግባት ወደ ጎል የመታውን በግብጠባቂው ሶፎንያስ የተመለሰውን ኳስ ድጋሚ አግኝቶ በፍጥነት ለመጣው እና ጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው ፍፁም ግርማ በጥሩ አጨራረስ በግራ እግሩ መረብ ላይ አሳርፎታል። ፍፁም ግርማ ዛሬ ያስቆጠረው ጎል  በኢትዮጵያ ፕሪሚየር የሊግ ውድድር ያስቆጠረው የመጀመርያው ጎል ሆኖ ተመዝግቧል።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በተወሰነ መልኩ ወረድ ያሉት መቐለ 70 እንደርታዎች አልፎ አልፎ ካልሆነ በቀር ወደፊት በመሄድ አደጋ ለመፍጠር ተቸግረው የመጀመርያው አጋማሽ ተገባዷል።

ከዕረፍት ሲመለስ ጨዋታው የጦና ንቦቹ በአብነት ደምሴ አማካኝነት በ50ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት ሁለተኛ ጎል ለማግኘት ተቃርበው ለጥቂት የግቡ ቋሚን ታኮ ወጥቶባቸዋል።

በመቐለ 70 እንደርታዎች በኩል ጎል ለማስቆጠር እና የጠራ የጎል ዕድሎችን ለመፍጠር ይቸገሩ እንጂ  በእንቅስቃሴ ደረጃ የተሻሉ የነበረ ቢሆንም በወላይታ ድቻ የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት በተደጋጋሚ ተጋላጭ ይሆኑ ነበር። ይህም ቢሆን በ62ኛው ደቂቃ ብሩክ ሙልጌታ ከግራ ወደ ውስጥ ቆርጦ የላከውን ኳስ ቦና አሊ በጎሉ ቅርብ ርቀት ደገፍ አድርጎ አገባው ሲባል ወደ ሰማይ የሰደዳት አጋጣሚ ለመቐለዎች የምታስቆጭ አጋጣሚ ነበረች።

አልፎ አልፎ ካልሆነ በቀር ጠንከር ያለ የጎል ሙከራዎች መመልከት ሳንችል የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ ሄዶ  በወላይታ ድቻ በኩል 73ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት ቴዎድሮስ ታፈሰ የመታውን ግብጠባቂው ሶፎንያስ ወደ ውጭ ያወጣው ይሄው ኳስ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን አብነት ደምሴ በግንባሩ የገጨውን በድጋሚ ግብጠባቂው ሶፎንያስ የመለሰው  በመጨረሻው ደቂቃዎች በጦና ንቦቹ አማካይነት የተፈጠሩ ዕድሎች ነበሩ።

በቀሩት ደቂቃዎች ወላይታ ድቻዎች ጨዋታውን በተገቢው መንገድ ተቆጣጥረው 1-0 በሆነ ውጤት አሸንፈው ወጥተዋል። በሁለተኛው ዙር በአራት ጨዋታ ሙሉ ነጥብ በማግኘት አስደናቂ ግስጋሴ እያደረጉ ያሉት ወላይታ ድቻዎች ደረጃቸውን ወደ ሁለተኝነት አሳድገዋል።