ሪፖርት |  ኢትዮጵያ መድን መሪነቱን ያጠናከረበትን ድል አስመዝግቧል

ሪፖርት |  ኢትዮጵያ መድን መሪነቱን ያጠናከረበትን ድል አስመዝግቧል

ኢትዮጵያ መድን ሀዋሳ ከተማን 2ለ1 በማሸነፍ መሪነቱን ማጠናከር ችሏል።

በኢዮብ ሰንደቁ

ምሽት 12 ሰዓት ሲል በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሜዳ በሀዋሳ ከተማ እና ኢትዮጵያ መድን መካከል የተጀመረው ጨዋታ ገና ጅማሮውን ባደረገበት በ3ኛው ደቂቃ ጎል ያስመለከተን ጨዋታ ነበር። ኢትዮጵያ መድኖች በቀኝ መስመር በመግባት ወደ ሳጥን የተሻገረለትን ኳስ አጥቂው መሐመድ አበራ ወደ ግብነት ቡድኑን ገና በመጀመሪያዎቹ ደቂቃ መሪ ማድረግ ችሏል።

ከግቡ መቆጠር በኋላ ሁለቱም ቡድኖች ፈጣን በሆነ ሽግግር ወደ ግብ መድረስ የቻሉ ሲሆን 14ኛው ደቂቃ ላይ ሐዋሳ ከተማዎች በአሊ ሱሌማን አማካኝነት የመጀመሪያ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ችለዋል።

ሐዋሳ ከተማዎች መሃል ሜዳ እና ወደ ሶስተኛው የሜዳ ክፍል ብልጫ በመውሰድ ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉ ቢሆንም 35ኛው ደቂቃ ላይ ግን ጥረታቸውን ያቀዘቀዘ ሁለተኛ ግብ ተቆጥሮባቸዋል። የማጥቃት መነሻቸውን ከቀኝ  ከመስመር ያደረጉት መድኖች ከቀኙ የሜዳ ክፍል የተሻማውን ኳስ አቡበከር ሳኒ ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን በሁለት ጎል ልዩነት መሪ ማድረግ ችሏል።

39ኛው ደቂቃ ላይ ግብጠባቂውን በማለፍ ያገኘውን ነፃ ኳስ ያልተጠቀመበት አሊ ሱሌማን ያደረገው ሙከራ ለሐዋሳ ከተማዎች እጅግ አስቆጪ ኳስ ነበር። 45ኛው ደቂቃ ላይ በኢትዮጵያ መድን በኩል ከቅጣት የተሻማው እና አለን ካይዋ በግንባሩ ሞክሮ የግቡ አግዳሚ የመለሰበት ሙከራ  ሌላኛው ጥሩ ሙከራ ነበር። ይህንንም ተከትሎ ጨዋታው በመድኖች 2-0 መሪነት ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል።

ከዕረፍት መልስ በብዙ ነገሮች ራሳቸውን አሻሻሽለው የቀረቡት ሐዋሳ ከተማዎች ጫና ፈጥረው በመጫወት ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል መድረስ የቻሉ ሲሆን ድካማቸውም ፍሬ አፍርቶ 54ኛው ደቂቃ ላይ ቸርነት አውሽ የመድን ተጫዋቾችን በማለፍ ከጎሉ ርቀት አክርሮ የመታውን ድንቅ በሆነ አጨራረስ ድንቅ የሆነ ጎል አስቆጥሮ የጎሉን ልዩነት ወደ አንድ ማጥበብ ችሏል።

ከግቡ መቆጠርም በኋላ በጥሩ መነሳሳት ጨዋታቸውን የቀጠሉት እና የአቻነት ግብ የፈለጉት ሀዋሳ ከተማዎች ጥሩ የሆነን መነቃቃትን ፈጥረዋል። ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ብልጫ ወስደው የተጫወቱት ሀዋሳዎች ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል በቁጥር በመብዛት መድረስ ቢችሉም ግን ጠንካራውን የመድን መከላከልን መስበር ተስኗቸው ጨዋታው በኢትዮጵያ መድን 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ይህንንም ተከትሎ ኢትዮጵያ መድን ከተከታዮቹ ያለውን የነጥብ ልዩነት ማስፋት ችሏል።