ባህር ዳር ከተማ ከሊጉ መሪ ላለመራቅ ስሑል ሽረ ደግሞ የነጥብ ልዩነቱን ለማጥበብ የሚፋለሙበት ጨዋታ የዕለቱ ቀዳሚ መርሐ-ግብር ነው።
የጣና ሞገዶቹ በመጨረሻዎቹ አራት የጨዋታ ሳምንታት ያስመዘገቧቸው ውጤቶች ወደ ዋንጫ ተፎካካሪነት አሸጋግረዋቸዋል። ከሦስት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ በማስመዝገብ ደካማ ብቃት ካሳዩባቸው መርሐግብሮች በኋላ በተከናወኑ አራት ጨዋታዎች ሦስት ድል እና አንድ የአቻ ውጤት ያስመዘገቡት ባህር ዳሮች ፋሲል ከነማ (2)፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሀዲያ ሆሳዕና የመሰሉ ጠንካራ ቡድኖች በገጠሙባቸው አራት ጨዋታዎች ያሳዩት ብቃት እና ያስመዘገቡት ውጤትም የሚያስወድሳቸው ነበር። ባለፉት አራት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው አስራ ሁለት ነጥቦች አስሩን በማሳካት በሚፈልጉት የውጤት ጎዳና ላይ የሚገኙት አሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛው ሊጉ በሀገራዊ ውድድሮች ከመቋረጡ በፊት በቡድናቸው ላይ የነበረው ሁለንተናዊ ጥንካሬ ማስቀጠል ቀዳሚ ስራቸው እንደሚሆን እሙን ነው።
በሰላሣ ሦስት ነጥቦች 3ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት
ባህር ዳሮች ካለው የነጥብ መቀራረብ አንጻር ከነገው ጨዋታ ሦስት ነጥብ ይዘው ካልተመለሱ ደረጃቸውን ሊያጡ የሚችሉበት ዕድል ስላለ በፉክክሩ ለመቀጠል ድል ማድረግ አስፈላጊያቸው ነው። በሊጉ ጥቂት ግቦች በማስተናገድ ፊት ላይ ከተቀመጡ ቡድኖች አንዱ የሆነው ቡድኑ በነገው ዕለት በመከላከሉ ረገድ ከባድ ፈተና ይገጥመዋል ተብሎ አይገመትም። በመጨረሻው ጨዋታ በሊጉ ፈታኝ መልሶ ማጥቃት ካላቸው ቡድኖች አንዱ የሆነው ሀዲያ ሆሳዕናን እንቅስቃሴ በመግታት ረገድ ውጤታማ ሥራ የሠሩት የአሰልጣኝ ደግአረግ ተጫዋቾች በአመዛኙ በሽግግሮች የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ለሚተጉት ስሑል ሽረዎች እጅ ይሰጣሉ ተብሎ ባይገመትም ለወትሮ በግብ ፊት ያላቸውን የአፈፃፀም ብቃት ከፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል።
በአስራ አምስት ነጥቦች 17ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ስሑል ሽረዎች ሀዋሳ ከተማ እና አዳማ ከተማ ነጥብ መጣላቸውን ተከትሎ የነጥብ ልዩነቱን የሚያጠቡበት ወርቃማ ዕድል አግኝተዋል።
ስሑል ሽረዎች በተለይም ውድድሩ በአዳማ ከተማ በተካሄደበት ወቅት በሁሉም ረገድ ደካማ ብቃት ማሳየታቸው ተከትሎ በወራጅ እንዲቀመጡ ሆኗል። ካለፉት አስር ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው ሰላሣ ነጥብ አራቱን ብቻ ያሳካው ቡድኑ በቀጣዮቹ መርሐግብሮች በብዙ ረገድ ተሻሽሎ መቅረብ ይገባዋል። በተለይም በመጨረሻዎቹ አምስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ያስቆጠረው የማጥቃት አጨዋወት በጨዋታዎቹ የሚፈጥራቸው የግብ ዕድሎች መጠን ከፍ ማድረግ እንዲሁም የተጫዋቾች የአፈፃፀም ድክመት ማረም የቡድኑ ቀጣይ የቤት ስራዎች ናቸው። አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት በነገው ዕለት ጥሩ የመከላከል ውቅር ያለው የመልሶ ማጥቃት ቡድን እንደመግጠማቸው ተደጋጋሚ ለጥቃት የሚጋለጠውን እና ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች መረቡን አስከብሮ መውጣት የተሳነው የመከላከል ጥምረት ማስተካከል እንዲሁም ወደ መከላከል በሚደርገው ሽግግር ድክመት የሚስተዋልበት አጨዋወታቸውን ማሻሻል ይኖርባቸዋል።
የሁለተኛው ዙር የመጀመርያ ድል ፍለጋ ወደ ሜዳ የሚገቡት ስሑል ሽረዎች በዝውውር መስኮቱ አብዲ ዋበላ፣ ኢቢሳ ከድር፣ አላዛር ሽመልስ እና ሄኖክ ፍቅሬን በማስፈረም ቡድናቸውን አጠናክረዋል።
በጣና ሞገዶቹ በኩል ሁሉም የቡድኑ አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ሲሆኑ ወሳኙ ተከላካይ ፍሬዘር ካሳም ከሁለት ጨዋታዎች ቅጣት መልስ ግልጋሎት እንደሚሰጥ ይጠበቃል። በስሑል ሽረ በኩልም በተመሳሳይ ሁሉም የቡድኑ አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።
የተሰረዘው የ2012 ጨዋታ ሳይጨምር በሊጉ ሦስት ጊዜ የተገናኙት ቡድኖቹ ባህር ዳር ከተማ ሁለት ጨዋታዎች ላይ ድል ሲያደርግ ስሑል ሽረ አንድ ጨዋታ አሸንፏል። በጨዋታዎቹ ባህር ዳር ከተማ 4 ግቦች ስያስቆጥር ስሑል ሽረ 1 አስቆጥሯል።