ሁለቱን የመዲናይቱ ክለቦች የሚያገናኘው ጨዋታ ሳምንቱ ተጠባቂ መርሐግብር ነው።
በአዳማ ከተማ በተከናወኑ ጨዋታዎች ላይ ደካማ ውጤት በማስመዝገብ በደረጃ ሰንጠረዡ ያሽቆለቆሉት መቻሎች ከስምንት የጨዋታ ሳምንታት በኋላ ዳግም ወደ አሸናፊነት ለመመለስ እና ደረጃቸው ለማሻሻል ነገን ይጠባበቃሉ።
በውድድር ዓመቱ መጀመርያ ለዋንጫ ከታጩ ክለቦች አንዱ የነበረው መቻል በአዳማ ከተማ ውጤታማ ጊዜ ማሳለፍ አልቻለም። በድሬዳዋ ከተማ የነበረውን ውጤታማ አጀማመር ማስቀጠል የተሳነው ቡድኑ በአዳማ ከተማ የአስር ሳምንታት ቆይታው ከአንድ የዘለለ ድል ማስመዝገብ ባለመቻሉም ከነበረበት የመሪነት ቦታ ርቆ በሰንጠረዡ አካፋይ ላይ ለመሰንበት ተገዷል።
ቡድኑ በፋሲል ከነማ አራት ለሁለት በተሸነፈበት የመጨረሻው ጨዋታ ከአራት መርሐግብሮች በኋላ ግብ ማስቆጠር ቢችልም አጠቃላይ የአዳማ ከተማ ቆይታው ሲገመገም እንደ ከዚህ ቀደሞቹ ጨዋታዎች ኳስን በሚገባ አለመቆጣጠሩ፣ ግልፅ የግብ ዕድሎች ለመፍጠር መቦዘኑ እና የአፈፃፀም ድክመቶች በጉልህ ታይቷል። ከምንም በላይ ደግሞ ዋነኛ ጥንካሬው የነበረው የማጥቃት አጨዋወቱ እና የግብ ማስቆጠር ብቃቱ ይዞ መዝለቅ አለመቻሉ የቡድኑ ድክመት ሆኖ አልፏል።
በሁለተኛው ዙር ከተከናወኑ ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው ዘጠኝ ነጥብ ሁለቱን ብቻ ያሳካው መቻል የውድድር ዓመቱ ጉዞው ለማቃናት እና ዳግም ወደ ዋንጫ ፉክክሩ ለመመለስ ድል ማድረግ አስፈላጊው ነው፤ ይህ እንዲሆን ደግሞ በቀዳሚነት ለግብ ማስቆጠር ችግሩ መፍትሔ ማበጀት ይኖርበታል። ቡድኑ ላለፉት አምስት ጨዋታዎች መረቡን ያላስደፈረው ጠንካራው ኢትዮጵያ ቡና እንደመግጠሙ የሚጠብቀው ፈተና ከባድ ይሆናል ተብሎ የሚገመት ቢሆንም ከቀናት በፊት በተካሄደው የኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታ ላይ ያሳየው ብቃት ማስቀጠል ከቻለ ግን ከጨዋታው ነጥብ ይዞ የሚወጣበት ዕድል ይፈጥራል።
ሰላሣ ሦስት ነጥቦች የሰበሰቡት ኢትዮጵያ ቡናዎች በሊጉ በጥሩ ወቅታዊ አቋም ከሚገኙ ክለቦች ይጠቀሳሉ። በአዳማ ውጤታማ የሚባል ቆይታ የነበረው ቡድኑ በመሃል በኢትዮጵያ መድን ከገጠመው ሽንፈት በስተቀር በርከት ላሉ ሳምንታት ከሽንፈት ርቆ ተከታታይ ድሎች ማስመዝገቡ ከመሪዎች ጎራ እንዲቀላቀል አስችሎታል። ኢትዮጵያ ቡና የተጋጋ እና የተደራጀ የመከላከል ውቅር ያለው ቡድን ነው፤ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች መረቡን ያላስደፈረው ቡድኑ በተለይም ከኳስ ውጭ ያለው ፋታ የለሽ እንቅስቃሴው ዋነኛ ጥንካሬው ነው። ከሦስት ተከታታይ ድሎች በኋላ ከሀዋሳ ከተማ ጋር ነጥብ የተጋሩት ቡናማዎቹ ዳግም ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ከመቻል ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ ጨምሮ በቀጣይ መርሐግብሮች የግብ ማስቆጠር ድክመታቸውን መፍታት ይጠበቅባቸዋል።
ሦስት ተከታታይ ድሎች እና ሁለት የአቻ ውጤት ባስመዘገባባቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ሦስት ግቦች ብቻ ያስቆጠረው ቡድኑ በዋንጫ ፉክክሩ ለመዝለቅ የአፈፃፀም ብቃቱን ማሳደግ ቀዳሚ ስራው መሆን ይኖርበታል።
ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በሊጉ 35 ጨዋታዎችን አድርገው ኢትዮጵያ ቡና 18 ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን መቻል 7 ጊዜ ድል አድርጎ በ10 ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። ቡናማዎቹ 54 ጦሩ ደግሞ 34 ግቦችን አስቆጥረዋል።