የ23ኛ ሳምንት የሦስተኛ ቀን ውሎ ባህር ዳር ከተማን ከስሑል ሽረ ያገናኘው ጨዋታ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተቋጭቷል።
በ22ኛ ሳምንት ባህር ዳር ከተማዎች በፍቅረሚካኤል ዓለሙ የመጨረሻ ደቂቃ አንድ ጎል ሀድያ ሆሳዕናን ከረቱበት ስብስባቸው ግርማ ዲሳሳ ፣ ፍፁም ፍትዓለሙ እና ፍቅረሚካኤል አለሙን አስወጥተው አምሳሉ ጥላሁን፣ ፍሬዘር ካሳ እና ጄሮም ፊሊፕን ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል ፤ ስሑል ሽረዎች በበኩላቸው በኢትዮ ኤሌክትሪክ አንድ ለምንም ከተሸነፉበት ስብስባቸው መሐመድ ሱሌማን፣ ክፍሎም ገብረህይወት፣ አሌክስ ኪታካ እና ሀብታሙ ገዛኸኝ በኢብሳ ከድር፣ ነፃነት ገብረመድህን፣ መሐመድ አብዱልላጢፍ እና በሄኖክ ተወልደ ተክተው ለጨዋታው ቀርበዋል።
ኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ በመሩት በዚህ ጨዋታ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴውን ብልጫ ለመውሰድ ጥረት ያደረጉት ባህርዳሮች በ5ኛው ደቂቃ ፊሊፕ ጄሮም ከተከላካይ ጀርባ የተጣለለትን ነፃ ኳስ አግኝቶ ኢላማውን ስታ የወጣችበት አጋጣሚ ቀዳሚዋ ሙከራ ነበረች።
ባህር ዳሮች በሙሉ ሀይላቸው በማጥቃት ወደ መሪነት ለመሸጋገር የሚያደርጉትን ጥረት ቀጥለው 29ሮም
ደቂቃ አማካይ ፍፁም አለሙ ብቻውን ከግብጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ያመከነው ለባህርዳሮች ቢያንስ የመጀመርያው አጋማሽ ሳይጠናቀቅ ጎል ማስቆጠር የሚችሉበት አጋጣሚ ነበር።
በስሑል ሽረዎች በኩል በመከላከሉ ላይ ስራ በዝቶባቸው ቢታይም በጥቂቱም ቢሆን የባህር ዳር መከላከል ቀጠናን ጥሶ በማለፍ አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። ይልቁንም አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት በቡድናቸው የኋላ ክፍል የመከላከል አደረጃጀትን ለማስተካከል የመሐል ተከላካይ ኢብሳ ከድርን በፍጥነት ለመቀየር ተገደዋል።
ያለ ጎል የተጠናቀቀው አጋማሹ ከዕረፍት ሲመለስ የጣና ሞገዶቹ ጎል አካባቢ ያለባቸውን የአጨራረስ ድክመት ይቀርፋሉ ተብሎ ቢጠበቅም አሁንም ካቆሙበት ነው የቀጠሉት። 47ኛው ደቂቃ ቸርነት ጉግሳ በቀላሉ ማስቆጠር የሚችለውን ዕድል ግብ ጠባቂው ሞይስ ፓዎቲ አጥብቦ ወጥቶ አምክኖበታል። ከዚች ሙከራ በኋላ ስሑል ሽረዎች የመከላከል አጥራቸውን በጥሩ አደረጃጀት አስጠብቀው በአንፃሩ ባህር ዳሮች በተደጋጋሚ ወደ ፊት በመሄድ የሚያደርጉት ጫና ተቀዛቅዘው የጨዋታው ደቂቃ ምንም ሙከራዎች ሳያስመለክተን ለውሃ ዕረፍት 70ኛው ደቂቃ መድረስ ችሏል።
የጨዋታው መልክ ፈጠን ካለ እንቅስቃሴ ወጥቶ በተለያዩ ምክንያቶች እየተቆራረጠ ቢቀጥልም 87ኛው ደቂቃ የስሑል ሽረ ተከላካይ ጥዑመልሳን እና ግብጠባቂው ሞይስ ኳሱን ለመቆጣጠር ሲገባበዙ ከመሐል ሾልኮ የገባው ወንደሰን በለጠ ወደ ጎል ቢመታውም ግብጠባቂው ሞይስ ወደ ውጭ አውጥቶበታል። በተጨማሪ ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ሄኖክ ይበልጣል ወደ ሰማይ የላካት የምታስቆጭ የጎል አጋጣሚ ተፈጥሮ ጨዋታው ያለምንም ጎል ተጠናቋል።