ሪፖርት | ተጠባቂው ጨዋታ በኢትዮጵያ ቡና አሸናፊነት ተጠናቋል

ሪፖርት | ተጠባቂው ጨዋታ በኢትዮጵያ ቡና አሸናፊነት ተጠናቋል

ቡናማዎቹ በአንተነህ ተፈራ ብቸኛ ግብ ታግዘው መቻልን 1-0 በማሸነፍ ከመሪዎቹ ያላቸውን የነጥብ ልዩነት አጥብበዋል።

በኢዮብ ሰንደቁ


ከሀገራት ጨዋታ መልስ ከተጀመረ ሦስተኛ ቀን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድሩን በሀዋሳ ዩንቨርስቲ ስታዲየም በማድረግ ምሽት 12 ሰዓት ሲል መቻልን ከ ኢትዮጵያ ቡና ያገናኘው መርሐግብር ተጠባቂ ጨዋታ ነበር። ጨዋታውም ተመጣጣኝ የሆነ የኳስ ፍሰት እና እንቅስቃሴ የነበረው ሲሆን የአጋማሹን የመጀመሪያ ደቂቃዎች በኳስ እና በማጥቃቱ ብልጫ ወስደው ሲጫወቱ የነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች የመጀመሪያ ሙከራቸውን በ22ኛው ደቂቃ በአንተነህ ተፈራ አማካኝነት ቢያገኙም ግን ግብ ጠባቂው ግብ ከመሆን ታድጓታል።

አጋማሹ ሊጠናቀቅ የቀሩትን 15 ደቂቃዎች በኢትዮጵያ ቡና የነበረውን የኳስ እና የጨዋታ ብልጫ የተረከቡት መቻሎች ልክ እንደ ቡናማዎቹ ፈጣን በሆነ ሽግግር ወደ ጎል መድረስ የቻሉ ሲሆን 44ኛው ደቂቃ ላይ አለምብርሃን ይግዛው በቀኝ መስመር ጠርዝ አካባቢ ከርቀት የመታው ኳስ የግቡን አግዳሚ ጨርፎ ወደ ውጭ ወጥቷል ይህም ለመቻሎች አስቆጪ ሙከራ ነበር። ይህንንም ተከትሎ የመጀመሪያው አጋማሽ ግብ ሳያስመለክተን ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ይበልጥ ተጋግሎ በቀጠለው ጨዋታ ከዕረፍት መልስ በማጥቃቱ ተሻሽለው የቀረቡት መቻሎች አስቆጪ እና ለጎል የቀረበ ሙከራን ማድረግ ችለው ነበር። 57 ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር የተሻማውን ኳስ ሽመልስ በቀለ በደረቱ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ አቤል ነጋሽ ለጎል ቅርብ ሆኖ ቢሞክርም የግቡን ቋሚ ገጭቶ ተመልሷል ያንን የተመለሰ ኳስ ያገኘው ዮሴፍ ታረቀኝ ቢሞክርም እሱም በተመሳሳይ የግቡን ቋሚ ገጭቶበታል።

ከዕረፍት መልስ ጥንቃቄን ምርጫቸው በማድረግ በጥቂት ቅብብሎች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል አልፎ አልፎ የሚደርሱት ኢትዮጵያ ቡናዎች 64ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ ቅብብል ወደ ጎል በመድረስ ኮንኮኒ ሀፍዝ ያቀበለውን ኳስ አንተነህ ተፈራ ወደ ግብነት በመቀየር ቡናማዎቹን መሪ ማድረግ ችሏል።


ከግቡ መቆጠር በኋላ በመቻሎች የአቻነት ግብ ፍለጋ በኢትዮጵያ ቡናዎች አልሸነፍም ባይነት ትንቅንቅ የቀጠለው ጨዋታ በመጨረሻም  ቡናማዎቹን ባለድል በማድረግ 1-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።