ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ሲዳማ ቡና

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ሲዳማ ቡና

በሁለት ነጥቦች የሚበላለጡ ቡድኖች ከስጋት ቀጠናው የሚያርቃቸው ድል ለማግኘት የሚፋለሙበት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።

ከስድስት ሽንፈት አልባ ጨዋታዎች በኋላ በመጨረሻው መርሐ-ግብር በኢትዮጵያ መድን ሽንፈት ያስተናገዱት የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በሀያ ስምንት ነጥቦች 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመጨረሻው ጨዋታ በመሪው ሽንፈት ብያስተናግድም በቅርብ  መርሐ-ግብሮች በብዙ መመዘኛዎች ጎልብቷል።
በተለይም ከ10ኛው ሳምንት ጀምሮ በተከታታይ አራት ጨዋታዎች ኳስና መረብ ማገናኘት ተስኖት የነበረው የማጥቃት አጨዋወቱ ግቦች ማስቆጠር መቀጠሉ እንዲሁም ጨዋታዎች የመቆጣጠር አቅሙ ከፍ ማድረጉ ቡድኑን ወደ ውጤት ጎዳና መልሶታል።

ከሁለተኛው ዙር ጅማሮ በኋላ ከተከናወኑ ሦስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው ዘጠኝ ነጥቦች ስድስቱን ያሳኩት ሀምራዊ ለባሾቹ በውጤት ረገድ ጥሩ ለውጦች ማስመዝገብ ቢችሉም አሁንም ከአደጋው ቀጠና አልራቁም፤ ከቅርብ ተፎካካርያቸው የሚያደርጉት እና ጠንካራ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ በሚገመተው የነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ይዞ መውጣት ያለው ትርጉም ትልቅ እንደመሆኑም ሊጉ ከመቋረጡ በፊት የነበሩ ጠንካራ ጎኖች ማስቀጠል እንዲሁም በመጨረሻው ጨዋታ በተቆጠሩባቸው ሁለት ግቦች ላይ የተስተዋሉ ግለ ሰባዊ ስህተቶች አርመው መቅረብ ይጠበቅባቸዋል።

ድል ካደረጉ አራት ጨዋታዎች ያለፋቸው ሲዳማ ቡናዎች በሀያ ስድስት ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

ከድሬዳዋ ከተማ እና ፋሲል ከነማ በመቀጠል በርከት ያሉ የአቻ ውጤቶች ያስመዘገቡት ሲዳማ ቡናዎች በመጨረሻዎቹ አራት የሊግ ጨዋታዎች ተከታታይ በአቻ ውጤቶች አስመዝገበዋል።
ቡድኑ በድሬዳዋ ከተማ ቆይታው በመጨረሻዎቹ አምስት ሳምንታት ከገጠሙት ተከታታይ ሽንፈቶች ማገገሙ እንደ አወንታ የሚጠቀስለት ነጥብ ቢሆንም ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ከማገባደድ አባዜው መላቀቅ ይኖርበታል።  ከመጨረሻዎቹ አስር መርሐ-ግብሮች ውስጥ በሰባቱ ነጥብ የተጋራው ቡድኑ የሁለተኛው ዙር አይን ገላጭ ድል ለማስመዝገብም በማጥቃት አጨዋወቱ በርከት ያሉ ለውጦች የማድረግ የቤት ስራ ይጠብቀዋል።
የቡድኑ የመከላከል አደረጃጀት በማስተካከል ረገድ ጥሩ ስራ የሰሩት አሰልጣኝ አዲሴ ካሳ በቀጣይም በመጨረሻዎቹ ስምንት ጨዋታዎች ሦስት ግቦች ብቻ ያስቆጠረው የማጥቃት ጥምረታቸው ድክመት መቅረፍ የሚያችል ስራ መስራት ግድ ይላቸዋል።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለ19 ጊዜያት የተገናኙ ሲሆን አመዛኙ 11 ጨዋታ በአቻ ውጤት የተጠናቀቀ ነው። ሲዳማ 5 ጨዋታ ሲያሸንፍ ንግድ ባንክ ደግሞ 3 አሸንፏል። በግንኙነታቸው ንግድ ባንክ 22፣ ሲዳማ ቡና ደግሞ 21 ግቦችን አስቆጥረዋል።