ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | አርባምንጭ ከተማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | አርባምንጭ ከተማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

በደረጃ ሰንጠረዡ በሁለት ነጥቦች ልዩነት የተቀመጡት አርባምንጭ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ የሚያገናኘው ጨዋታ የሳምንቱ መገባደጃ መርሐ-ግብር ነው።

በመጀመርያው ዙር የመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎች ላይ አንድ ሽንፈት እና ሁለት የአቻ ውጤቶች ካስመዘገቡ ወዲህ በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ድል አድርገው ወደ ሰንጠረዡ አናት መጠጋት ችለው የነበሩት አርባምንጭ ከተማዎች በመጨረሻው ጨዋታ በመቐለ 70 እንደርታ ከገጠማቸው ሽንፈት አገግመው ደረጃቸውን ለማሻሻል ወደ ሜዳ ይገባሉ። 

ሊጉ በድሬዳዋ ከተማ በተካሄደበት ወቅት ከፍተኛ የወጥነት ችግር የነበረበት የአዛዎቹ ስብስብ በአዳማ ከተማ ውጤታማ ጊዜ ማሳለፍ ችሏል።
ሽንፈቶች መቀነሱ፣ በበርካታ ጉዳቶች በተፈተነበት ወቅት በጠባብ አማራጭ እንደ ቡድን ጥሩ መንቀሳቀሱ እንዲሁም በማጥቃቱ ረገድ ያሳየው እመርታም የዚህ ማሳያ ናቸው። በተለይም በድሬ የአስር ሳምንታት ቆይታው 8 ግቦች ካስቆጠረ በኋላ በአዳማ ቆይታው ትልቅ መሻሻል አሳይቶ በአስር ጨዋታዎች 15 ያስቆጠረው  የማጥቃት አጨዋወት የቡድኑ ዋነኛ ጥንካሬ ነው። አዞዎቹ በመጨረሻው የሊግ ጨዋታ ሽንፈት ብያስተናግዱም የሜዳ እንቅስቃሴያቸው ለክፉ የሚሰጥ አልነበረም፤ በነገው ዕለትም በረዥም ጊዜ ጉዳት የነበሩት አሸናፊ ተገኝ እና ሳሙኤል አስፈሪ እንዲሁም ቅጣት ላይ የነበረው አሸናፊ ፊዳ መመለሳቸው ለአሰልጣኝ በረከት ደሙ ጥሩ ዜና ነው።

ሀያ ስምንት ነጥቦች ሰብስበው በ10ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ደረጃቸውን ለማሻሻል በሁለት ነጥቦች ልቆ ከተቀመጠው አርባምንጭ ከተማ ጋር ይፋለማሉ።

በሁለተኛው ዙር በተካሄዱ  ሦስት ጨዋታዎች በሁለቱ ሽንፈት የገጠመው ኤሌክትሪክ በሁለት ነጥብ ከሚልቀው የነገ ተጋጣሚው ሙሉ ነጥብ ማግኘት ብያንስ ሦስት ደረጃዎች እንዲያሻሽል ይረዳዋል። ቡድኑ ከሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች አገግሞ በመጨረሻው ጨዋታ ስሑል ሽረን መርታት ቢችልም በስጋት ቀጠናው ላይ ከሚታየው የነጥብ መቀራረብ አንፃር  ሽንፈት ማስተናገድ ወደ ኋላ ሊያስቀረው ሰለሚችል ለጨዋታው ከፍ ያለ ትርጉም ሰጥቶ ወደ ሜዳ ይገባል ተብሎ ይገመታል። ከዚህ ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ይዞ መውጣት ለሁለቱም ቡድኖች ተቀራራቢ ትርጉም ያለው ቢሆንም በወራጅ ቀጠናው አፍፋ ካሉ ቡድኖች በሦስት ነጥብ ብቻ ልቀው ለሚገኙ ኤሌክትሪኮች ግን ይበልጥ ከፍ ያለ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ ቡድኑ ከወትሮው በተለየ ተነሳሽነው እና ብቃት ወደ ሜዳ መግባት ይኖርበታል።

በተለይም ተከታታይ አራት ድሎች ባስመዘገበበት ወቅት ስምንት ግቦች ማስቆጠር ችሎ የነበረው የቡድኑ የማጥቃት ክፍል በመጨረሻ ሳምንታት ከገጠመው መጠነኛ መንገራገጭ ማገገም ይጠበቅበታል፤  ከዚህ በተጨማሪም ተጋጣሚው ከሊጉ ሦስት ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ቡድኖች አንዱ እንደመሆኑ በመከላከሉ ረገድ የሚጠብቀው ፈተና ቀላል ላይሆንለት ይችላል።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 17 ጊዜ ተገናኝተዋል። ኤሌክትሪክ 7 ሲያሸንፍ አርባምንጭ 5 አሸንፏል፤ አምስት ጨዋታ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ኢትዮ ኤሌክትሪክ 22 አርባምንጭ ከተማ ደግሞ 20 ማስቆጠር ችለዋል።