በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ በተካሄደው ጨዋታ ሲዳማ ቡና በሜዳው እና በደጋፊው ፊት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2-1 ተሸንፏል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከባለፈው የኢትዮጵያ መድን 2-1 ሽንፈት ማግስት የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ግብጠባቂውን ፓልክ ቾል፣ ዮናስ ለገሰ እና አዲስ ግደይ ወጥተው ግብጠባቂ ፍሬው ጌታሁን፣ ተመስገን ተስፋዬ ሃይከን ደዋሙ ተክተዋል። ሲዳማ ቡና በአንፃሩ ከአዳማ ከተማ ነጥብ ከተጋሩበት ጨዋታ የአምስት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል። ጊት ጋትኩት፣ ኢማኑኤል ሳባን፣ አበባየሁ ሀጂሶ፣ ሳሙኤል ሳሊሶ እና ማይክል ኪፖሩቪ በማሳረፍ ለያሬድ ባዬ፣ ዮሴፍ ዮሐንስ፣ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን፣ መስፍን ታፈሰ እና ይገዙ ቦጋለ የመጀመርያ አሰላለፍ ዕድል ሰጥቷል።
እጅግ በርካታ ደጋፊዎች ተገኝተውበት ፌደራል ዳኛ ሃይማኖት አዳነ በመሩት በዚህ ጨዋታ የመጀመርያዎቹ አስራ አምስት ደቂቃ በሁለቱም በኩል ለጎል የቀረበ ሙከራ ባይደረግበትም ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በአጫጭር ቅብብሎች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመግባት ቢቸገሩም በ17ኛው ደቂቃ በመጀመርያ ሙከራቸው ጎል አስቆጥረዋል። ከቀኝ መስመር ጠርዝ በኩል ከርቀት የተሰጠውን ቅጣት መት ኤፍሬም ታምራት ወደ ጎል ያሻገረውን ሳይመን ፒተር በግንባሩ በመግጨት ኳሷን ቆርጦ መረቡ ላይ አሳርፎታል።
ባለሜዳዎቹ ከጨዋታው ጅማሮ አንስተው ተጭነው እንደመጫወታቸው ቀደመው ጎል ያስቆጥራሉ ተብሎ ቢታሰብም ጎል ከተቆጠረባቸው በኋላ ቢሆን ተደጋጋሚ የጠሩ የጎል ዕድሎችን ባይፈጥሩም ወደ ጨዋታው ለመግባት በሙሉ አቅማቸው ጫና ፈጥረው ተጫውተዋል በዚህ ሂደትም በ43ኛው ደቂቃ ሀብታሙ ታደሰ ከተከላካይ ጀርባ የጣለለትን ነፃ ኳስ ይገዙ ቦጋለ አግኝቶ ኳሷን ወደ ላይ የሰደዳት ለባለሜዳዎቹ ወደ ጨዋታው እንዲገቡ የምታስችል ጥሩ አጋጣሚ ነበረች። ሀምራዊ ለባሾቹ ጎሉን ከማስቆጠራቸው ውጭ መጠነኛ በሆነ ከሚያደርጉት የኳስ ንክኪ ውጭ በራሳቸው ሜዳ ክፍል በቁጥር በዝተው ሲከላከሉ አርፍደው አንድ ለምንም እየመሩ አጋማሹ ተጠናቋል።
መጠነኛ ዝናብ እየዘነበ ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ ሲዳማ ቡናዎች በአጋማሹ ለነበራቸው ብልጫ መልስ የምትሰጥ ጎል በ49ኛው ደቂቃ አግኝተዋል። ጎሉንም ዮሴፍ ዮሐንስ ከሳጥን ውጭ በግሩም ሁኔታ አስቆጥሮታል። በፍጥነት ጎሉ መቆጠሩን ተከትሎ የተነቃቁ የሚመስሉት ቡናማዎቹ የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን ተጫዋቾች ቀይረው በማስገባት ተጨማሪ ጎል ፍለጋ ጥረት ማድረጋቸውን ቢቀጥሉም አጋጣሚዎችን በመፈጠር ኩል ውስንነት ታይቶባቸዋል።
በአንፃሩ ንግድ ባንኮች በመረጡት ጥንቃቄ በተሞላበት እንቅስቃሴ ምክንያት በተደራጀ ሁኔታ አደጋ ለመፍጠር አልቻሉም።
የጨዋታው 73ኛው ደቂቃ ላይም በዛብህ መለዮ
ሳጥን ውሰጥ በግራ ጠርዝ መስፍን ታፈሰ
ያደረጉትን ሙከራ ግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን የመለሰበት የግብ ዕድል በተጨማሪ 83ኛው ደቂቃ በቅብሎች መሐል ከሳጥን ውጭ ኳሱን ያገኘው ፍቅረየሱስ በግራ እግሩ አክሮ የመታውን በድጋሚ ግብ ጠባቂው ፍሬው ያዳነበት የምታስቆጭ ወርቃማ አጋጣሚ ነበረች።
በቀሪው ደቂቃዎች ጨዋታው በአንድ አቻ ውጤት ይጠናቀቃል ተብሎ ሲጠበቅ ድራማዊ በሆነ መንገድ ንግድ ባንኮች 90+2 በተጨማሪ ደቂቃ የማሸነፊያ ጎል አግኝተዋል።
በመልሶ ማጥቃት ከቀኝ መስመር ሳይመን ፒተር በጥሩ መንገድ ያሻገረለትን ተቀይሮ የገባው ወጣቱ አጥቂ ዳዊት ዮሐንስ በድንቅ አጨራረስ በግንባሩ ገጭቶ ኳሷን መረቡ ላይ አሳርፎት ቡድኑን ደስታ ውስጥ ከቷቸዋል። ውጤቱም ዘጠና ደቂቃውን ሙሉ ጫና ፈጥረው ለተጫወቱት ሲዳማ ቡና ተጫዋቾች እና ደጋፊዎች አንገት ሲያስደፋ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ጣፋጭ ድል ሆኖ ጨዋታው 2-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።