አርባምንጭ ከተማን ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ያገናኘው የሳምንቱ የመጨረሻ መርሐግብር በአርባምንጭ አሸናፊነት ተጠናቋል።
በኢዮብ ሰንደቁ
የሳምንቱ መርሐግብር መዝጊያ የነበረው እና አርባምንጭ ከተማን ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ያገናኘው የምሽቱ ጨዋታ አርባምንጭ ከተማዎች በእንቅስቃሴ ረገድ የተሻሉበት ነበር። በረጃጅም የኳስ ንክኪዎች ወደ ተጋጣሚ ግብ ለመድረስ ሙከራ ያደርጉ የነበሩት አዞዎቹ በ4ኛው ደቂቃ ላይ ቡታቃ ሽመና ሰንጥቆ የሰጠውን ኳስ አህመድ ሁሴን ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
12ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮ ኤሌክትሪኩ ተከላካይ ጌታሁን ባፋ ወደ ኋላ መልሶ ለግብ ጠባቂው ለመመለስ የሞከረው ኳስ በተጫዋቾቹ አለመግባባት ምክንያት አርባምንጮችን መሪ ያደረገ ጎል ተቆጥሯል።
የግቡ መቆጠር መነቃቃትን የፈጠረባቸው ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በተሻለ እንቅስቃሴ የአቻነት ግብ ፍለጋ ሲታትሩ ተስተውለዋል። በአንድ ግብ ብቻ ማፈግፈግን ያልፈለጉት አርባምንጭ ከተማዎችም በቡታቃ ሸመና፣ ፍቃዱ መኮንን እና አህመድ ሁሴን አማካኝነት ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ማድረግ የቻሉ ቢሆንም በግብ ጠባቂው ጥረት ጎል ከመሆን ድነዋል። ጨዋታውም በአርባምንጭ 1-0 መሪነት ወደ ዕረፍት አምርቷል።
ሁለተኛው አጋማሽ ላይ የአቻነት ግብን ፍለጋ ተሻሽለው የቀረቡት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ወደ ጎል በመድረስ ረገድ የተሻሉ ነበሩ። ነገር ግን የአርባምንጭን የመከላከል አጥር መናድ ተስኗቸው ተስተውሏል።
ረዘም ያሉ ደቂቃዎችን ያለምንም ሙከራ ያስመለከተን ጨዋታ የኋላ ኋላ የኢትዮ ኤሌክትሪኮችን ነጥብ ይዞ የመውጣት ተስፋ የሰበረ ጎል አርባምንጭ ከተማዎች 85ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥረዋል። በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው ቡታቃ ሸመና በድንቅ ዕይታ ሰንጥቆ የሰጠውን ኳስ ታምራት ኢያሱ ወደ ግብነት ቀይሮ አዞዎችን በሁለት ጎል ልዩነት መሪ ማድረግ ችሏል። ይህንንም ተከትሎ አርባምንጭ ከተማ 2-0 በሆነ ውጤት ኢትዮ ኤሌክትሪክን ማሸነፍ ችሏል።