የፋይናንስ አሰራር ተቆጣጣሪ ኮሚቴ ባሰተላለፈባቸው ውሳኔ ቅጣት የተላለፋባቸው የተወሰኑ ተጫዋቾች እና ክለቦች ጉዳያቸውን ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት ወስደውታል።
የፋይናንስ አሰራር ተቆጣጣሪ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የክለቦች የክፍያ ስርዓት አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 1/2016 በአንቀጽ 7 በተሰጠው ሃላፊነት መሰረት በአራት ክለቦች እና በ15 ተጫዋቾች ላይ ባደረገው ምርመራ ክለቦቹ የቅድመ ክፍያ(በሦስተኛ ወገን) በመክፈላቸው እና ተጫዋቾቹ በመቀበላቸው በአንቀጽ 5 የተከለከሉ ተግባራት ስር የተቀመጡትን ድንጋጌዎች ጥሰዋል በሚል በመቻል፣ ሲዳማ ቡና፣ ሀዋሳ ከተማ፣ መቐለ 70 እንደርታ በክለቦቹ እና በተጫዋቾቹ ላይ የቅጣት ውሳኔ መተላለፍ ይታወቃል።
ውሳኔው የተላለፈባቸው አካላት የይግባኝ አቤቱታቸውን በደብዳቤ መጠየቃቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ የቅጣት ውሳኔው ታግዶ እንዲቆይ ካደረገ በኋላ ሰሞኑን ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ጉዳዮን ሲመረምር ቆይቶ አቤቱታቸው ውድቅ እንዲሆን እና ኮሚቴው ሰጥቶ የነበረው ዕግድ እንዲነሳ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።
አሁን ደግሞ በሲዳማ ቡና እና በመቻል በኩል ያቀረቡት የይግባኝ አቤቱታ ውድቅ እንዲሆን ከተደረገባቸው በኋላ የህግ ባለሙያ በመቅጠር ጉዳያቸውን ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት ይዘው በመሄድ ክስ መመስረታቸውን እና አቤቱታቸውን ፍርድ ቤቱ እንዳየው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል። ጉዳዮንም በፌደራል የመጀመርያ ፍርድ ቤት የንግድና ኢንቨስትመንት ምድብ 3ኛ ንግድ ችሎትም አክስዮን ማህበሩ የሰነድ የመከላከያ መልሳቸውን ለሚያዚያ 14 እንዲያቀርቡ ታዘዋል።
በጉዳዩ ዙርያ የሚኖሩ አዳዲስ መረጃዎችን እየተከታተልን የምናቀርብ ይሆናል።