በአንድ ነጥብ ልዩነት በደረጃ ሰንጠረዡ ተከታትለው የተቀመጡት ዐፄዎቹ እና ፈረሰኞቹ የሚያፋልመው መርሐ-ግብር የጨዋታ ሳምንቱ መክፈቻ ነው።
በመጨረሻው ጨዋታ ወልዋሎን በማሸነፍ ወደ ሰንጠረዡ አጋማሽ ያሻገራቸውን ድል ያገኙት ፋሲል ከነማዎች በሰላሣ ነጥብ 9ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
ፋሲል ከነማዎች በተለይም ባለፉት ሦስት መርሐ-ግብሮች የሚታይ መሻሻል አሳይተዋል። ተከታታይ ሽንፈት ካስመዘጉበት ወቅት በኋላ በተከናወኑ ሦስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው ዘጠኝ ነጥቦች ሰባቱን ያሳኩት ዐፄዎቹ በተለይም በማጥቃቱ ረገድ ያሳዩት ጉልህ መሻሻል በዋናነት ይጠቀሳል።ሁለት ሽንፈት እና አንድ የአቻ ውጤት ባስመዘገቡባቸው መርሐ-ግብሮች አንድ ግብ ብቻ ያስቆጠሩት ፋሲሎች በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ግን ስድስት ግቦች ማስቆጠር ችለዋል፤ ይህም በሰባት ተከታታይ መርሐ-ግብሮች ካስቆጠሩት ድምር የግብ መጠን የሚልቅ ነው።
በፋሲል ከነማ በኩል የሚታየው ሌላው ጠንካራ ጎን የቆመ ኳስ አጠቃቀማቸው ነው፤ በውድድር ዓመቱ በርከት ያሉ ግቦች ከቆመ ኳስ ያስቆጠረው ቡድኑ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎችም ሦስት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል። ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ሦስት ግቦች አስቆጥሮ አንድ ግብ የሆነ ኳስ አመቻችቶ ያቀበለው አምበሉ ጌታነህ ከበድ ወደ ጥሩ ብቃት መምጣቱም የማጥቃት ክፍሉን አጎልብቶታል።
በሰላሣ አንድ ነጥቦች 8ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከሁለት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች መልስ ወደ ድል መንገድ ለመመለስ በአንድ ነጥብ አንሶ 9ኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው ፋሲል ከነማ ይጫወታሉ።
ፈረሰኞቹ በ17ኛው ሳምንት ወላይታ ድቻን ሁለት ለባዶ ካሸነፉ በኋላ ከድል ጋር ተራርቀዋል። ቡድኑ ባለፉት ስድስት የጨዋታ ሳምንታት ሙሉ ነጥብ አለማግኘቱም ከነበረበት የመሪዎቹ ጎራ አሽቆልቁሎ በሰንጠረዡ አካፋይ እንዲቀመጥ ሆኗል። ለዚህ እንደዋነኛ ምክንያት የሚነሳው ዳግሞ የቡድን የግብ ማስቆጠር ችግር ነው፤ ቡድኑ በአዳማ ከተማ በተካሄዱ የመጀመርያ ስድስት ጨዋታዎች ላይ አስር ግቦች ማስቆጠር ቢችልም ቀጥለው በተካሄዱ ስድስት ጨዋታዎች ላይ ማስቆጠር የቻለው የግብ መጠን ግን አንድ ብቻ ነው። ይህም ቡድኑ በግብ ማስቆጠሩ ረገድ ምንያህል እንደተዳከመ ግልፅ ማሳያ ነው። አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የቀደመው የማጥቃት ጥንካሬያቸው መመለስ ቀዳሚ የቤት ስራቸው መሆን ይገባዋል፤ በመጨረሻው ጨዋታ በርከት ያሉ ለውጦች ያደረጉት ፈረሰኞቹ በነገው ጨምሮ በቀጣይ መርሐ-ግብሮች ንፁህ የግብ ዕድሎች በመፍጠርም ሆነ ግብ በማስቆጠር ረገድ ያሉባቸው ድክመቶች መቅረፍ ይኖርባቸዋል።
በፋሲል ከነማ በኩል ሀቢብ መሐመድ ፣ አፍቅሮተ ሠለሞን እና ተመስገን ካስትሮ ባልታወቀ ምክንያት አሁንም ከክለቡ ጋር የሉም፤ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ግን ሻይዱ ሙስጠፋ፣ ተገኑ ነጋሽ፣ ፍሪምፖንግ ክዋሜ እና አብዱልአዚዝ ቶፊክ በጉዳት ምክንያት ወደ ሀዋሳ ያልተጓዙ ተጫዋቾች ናቸው።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በፕሪሚየር ሊጉ ለ16 ጊዜያት የተገናኙ ሲሆን 37 ግቦች በተቆጠሩበት ግንኙነታቸው 15 ግቦችን ያስቆጠረው ፋሲል ከነማ ለ7፤ 22 ግቦችን ያስቆጠረው ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ በተመሳሳይ ለ7 ጊዜ ድል ሲቀናው ሁለቱ ጨዋታዎች በአቻ ተጠናቀዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ 2000 ዓ.ም ላይ የ 2-0 ፋሲል ከነማ ደግሞ 2011 ዓ.ም ላይ የ 3-0 የፎርፌ ውጤት አግኝተዋል።