ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ወልዋሎ ዓ.ዩ ከ ኢትዮጵያ መድን

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ወልዋሎ ዓ.ዩ ከ ኢትዮጵያ መድን

በሊጉ ግርጌ እና አናት በመቀመጥ በሁለት የተለያየ መንገድ በመጓዝ ላይ የሚገኙ ቡድኖች የሚያገናኘው ጨዋታ የዕለቱ ሁለተኛ መርሐ-ግብር ነው።

በደካማ የውድድር ዓመት እዚህ የደረሱት ወልዋሎዎች በእንቅስቃሴ ረገድ በቅርብ ሳምንታት በአንፃራዊነት ውስን መሻሻሎችን ማሳየት ቢችሉም
ከሰባት የጨዋታ ሳምንታት በኋላ ዳግም ወደ ተከታታይ ሽንፈት ተመልሰዋል።

በዘጠኝ ነጥቦች ግርጌው ላይ የተቀመጠው ቡድኑ በዝውውር መስኮቱ አጋማሽ ስድስት ተጫዋቾች በማስፈረም ባለፉት መርሐ-ግብሮች ሽግሽግ በማድረግ ጭምር ሙከራዎችን ቢያደርም የውድድር ዓመቱ ሁለተኛ ድል ማሳካት አልቻለም።

በሊጉ ጥቂት ግቦች በማስቆጠርም ሆነ በርከት ያሉ ግቦች በማስተናገድ ከፊት ከተቀመጡ ክለቦች ውስጥ የሚገኙት ቢጫዎች ከተጋጣሚያቸው ጥንካሬ አንፃር በነገው ጨዋታ ከባድ ፈተና እንደሚጠብቃቸው እሙን ነው፤ በተለይም ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች አምስት ግቦች ያስቆጠረው የመድን የማጥቃት ጥምረት ማቆም በጨዋታው የሚጠብቃቸው ትልቁ ስራ ነው።

ወልዋሎዎች እንደ ቡድን ተደራጅቶ በመንቀሳቀስም ይሁን ትርጉም ያላቸው የማጥቃት ሂደቶችን በማሳየት ረገድ ቀስ በቀስም ቢሆን አንፃራዊ መሻሻሎች ማሳየታቸው ባይካድም በነገው ዕለት በውድድር ዓመቱ ስምንት ግቦች ብቻ ካስተናገደው ጠንካራው የመድን ተከላካይ ክፍል የሚጠብቃቸው ፍልምያ ጨዋታውን ከባድ ያደርግባቸዋል። ለከርሞ በሊጉ ለመቆየት ከባድ ስራ የሚጠብቃቸው ቢጫዎቹ በተደጋጋሚ ቡድኑን ዋጋ ያስከፈለው ግለ-ሰባዊ ስህተት አርሞ መቅረብም ይጠበቅባቸዋል።

አርባ አራት ነጥቦች ሰብስበው ሊጉን በመምራት ላይ የሚገኙት ኢትዮጵያ መድኖች መሪነታቸው ይበልጥ ለማደላደል በሊጉ ግርጌ የተቀመጠውን ወልዋሎ ይገጥማሉ።

ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች አሸንፎ ከተከታዮቹ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ስምንት ያደረሰው የሊጉ መሪ በሰንጠረዡ የላይኛው ክፍል ላይ ባለው ፉክክር ወሳኝ የሆነውን ጨዋታ ያደርጋል። በሁሉም መመዛኛዎች ሲታይ ጥሩ የውድድር ዓመት በማሳለፍ የሚገኙት መድኖች በሁለተኛው ዙር የመጀመርያ ጨዋታ ላይ በወላይታ ድቻ ከገጠማቸው ሽንፈት በማገገም ሦስት ተከታታይ ድሎች አስመዝግበው በዋንጫ ፉክክሩ አንድ እርምጃ ወደ ፊት ሄደዋል።

በውድድር ዓመቱ ጉዟቸው የጎላ ድርሻ ያላቸው ተጫዋቾች ቢኖሩም የአሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌው ስብስብ ዋነኛ ጥንካሬው እንደ ቡድን የሚያደርገው እንቅስቃሴ ነው። በውድድር ዓመቱ ጥቂት ግቦች ያስተናገደው ጠጣሩ የተከላካይ ጥምረት፤ በታታሪ ተጫዋቾች የተገነባው የአማካይ ክፍል እንዲሁም በርካታ ግቦች በማስቆጠር በሊጉ ቀዳሚ የሆነው የማጥቃት ክፍል ያላቸው ድርሻ ተመጣጣኝ መሆኑም የዚህ ማሳያ ነው። ጠንካራ ቡድኖች በገጠሙባቸው የመጀመርያው ዙር የመጨረሻ ሳምንታት የዋንጫ ፉክክሩን መልክ የለወጡ ወሳኝ ድሎች በማግኘት በመሪነቱ የተደላደሉት መድኖች በነገው ጨዋታ ከባድ ፈተና ይገጥማቸዋል ተብሎ ባይገመትም ዕድሎች በመጠቀም ረገድ የነበሩበትን ክፍተቶች ቀርፎ በጥሩ ብቃት የሚገኘውን የፊት መስመር ጥምረታቸው ጥንካሬ ዘላቂ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

በወልዋሎ በኩል ዩጋንዳዊው ሙሳ ራማታህ በቅጣት፤ በረከት አማረ እና ኤፍሬም ኃይለማርያም ደግሞ በጉዳት ምክንያት በነገው ጨዋታ አያሰለፉም። በመድን በኩል ደግሞ ሚልዮን ሰለሞን እና ረመዳን የሱፍ በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ ናቸው።

ነገ በፕሪምየር ሊግ ታሪካቸው ለሁለተኛ ጊዜ የሚገናኙት ቡድኖቹ በመጀመርያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ኢትዮጵያ መድን በአብዲሳ ጀማል ብቸኛ ግብ ማሸነፉ ይታወሳል።