👉 “የአስተያየት መስጫ ሳጥንን መዝጋት ስታዲየም ላይ ጨዋታ ሊያይ የገባን ተመልካች አታውራ ፤ አትተንፍስ እንደማለት ነው። ስለዚህ…”
👉 “…ከዚህ በኋላ ግን ያንን ቁጥጥር የምናደርግ ይሆናል።”
👉 ሶከር ኢትዮጵያ ባደረገችው ማጣራት የአክሲዮን ማኅበሩ ፔጅ በጊዜያዊነት እንዲታገድ ያስቻለው ጨዋታ….
የሊጉ የበላይ አካል ጨዋታዎችን በፌስቡክ ገፁ እንዳያስተላልፍ የታገደበትን ሂደት እና አጠቃላይ ከጨዋታዎቹ የቀጥታ ስርጭት ጋር ተያይዞ የተፈጠሩትን ነገሮች በተመለከተ ማጣራት አድርገናል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር በሊጉ የምስል መብት ባለቤት ሱፐር ስፖርት የቀጥታ ስርጭት ሽፋን የማያገኙ ጨዋታዎችን በማኅበራዊ ትስስር ገፁ (በፌስቡክ) በቀጥታ ስርጭት ሲያስተላልፍ መቆየቱ ይታወቃል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ማኅበሩ ዛሬ በማለዳ የ24ኛ ሳምንት የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ቀን ጨዋታዎችን እንዳያስተላልፍ በፌስቡክ መታገዱን ይፋ አድርጓል። ታዲያ ይህ ጉዳይ በማኅበራዊ ሚዲያ ከፍተኛ መነጋገሪያ መሆኑን በመረዳት ሶከር ኢትዮጵያ ምን እንደተፈጠረ የአክሲዮን ማኅበሩን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ሙሉጌታ ደሳለኝ አዋርታለች።
“ዘንድሮ በጣም በርካታ ጨዋታዎች ናቸው በሊጉ የሚደረጉት። የሊጉ የምስል መብት ባለቤት ሱፐር ስፖርት 72 ጨዋታዎችን ብቻ ነው አስተላልፋለው ያለውና እኛ ለስፖርት ቤተሰቡ አማራጭ ለመሆን በማኅበራዊ ገፃችን ጨዋታዎችን እያስተላለፍን እንገኛለን። ጨዋታዎቹን የምናስተላልፈው ገቢ ለማግኛ አይደለም። ምክንያቱም የምስል መብት ያለው ተቋም ያንን ስለማይፈቅድልን። ስለዚህ በዩ ቱብ እና በሌሎች አማራጮች ጨዋታውን ማሰራጨት አንችልም። ይህ በእንዲህ እንዳለ የ23ኛ ሳምንት ጨዋታ ላይ ከደጋፊዎች የእርስ በእርስ መሰዳደብ ጋር ተያይዞ በፌስቡክ ኮሚኒቲ ስታንዳርድ ያፈነገጡ የጥላቻ ድርጊቶች ስለነበሩ ትናንትን ጨምሮ ለሦስት ቀናት ጨዋታ እንዳናስተላልፍ ታግደናል።” ያሉት አቶ ሙሉጌታ ከዚህ ቀደም መሰል ድርጊቶች ለሁለት ጊዜያት ያህል አጋጥሞ እንደነበር አውስተዋል።
ከዚህ በፊት ያጋጠሙት ችግሮች ከኮፒ ራይት ጋር ተያይዞ እንደነበረና ማኅበሩ መፍትሄ ለመስጠት አንድ ተለዋጭ የፌስቡክ ፔጅ እንደከፈተ ግን ፌስቡክ ባለው መስፈርት አንድ የተከፈተ ፔጅ ወዲያው ላይቭ ማስተላለፍ ስለማይፈቀድለት አማራጩ እንዳልተሳካ አብራርተዋል። አሁንም በዛ አማራጭ ጨዋታዎቹን እንዳይተላለፉ አዲሱ ፔጅ በተመሳሳይ ስም እና ባለቤት ስር ስለሆነ እንዳልተቻለ ገልፀዋል።
አቶ ሙሉጌታ ቀጥለው “ከኮፒ ራይት ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር በሚገባ እየፈታን መጥተናል። አሁን ደግሞ ያጋጠመው ከአስተያየት መስጫ ሳጥን ጋር ተያይዞ ያለ ነገር ነው። የአስተያየት መስጫ ሳጥንን መዝጋር ስታዲየም ላይ ጨዋታ ሊያይ የገባን ተመልካች አታውራ አትተንፍስ እንደማለት ነው። ስለዚህ ፊልተር ማረግ ነው የሚጠበቅብን እንጂ አታውራ ማለቱን አናምንበትም። ከዚህ በኋላ ግን ያንን ቁጥጥር የምናደርግ ይሆናል።” ብለውናል።
ሶከር ኢትዮጵያ ባደረገችው ማጣራት የአክሲዮን ማኅበሩ ፔጅ በጊዜያዊነት እንዲታገድ ያስቻለው ጨዋታ የወላይታ ድቻ እና መቐለ 70 እንደርታ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።
በመጨረሻም እገዳው እስኪነሳ ድረስ እንደተለመደው ጨዋታዎቹ እንደሚቀረፁ እና ጨዋታው እንደተጠናቀቀ ሀይላይት እንዲሁም ጨዋታው እየሄደ ጎሎችን ቶሎ ቶሎ እንደሚለቀቁ ተጠቁሟል።