ሪፖርት | ተጠባቂው ጨዋታ በፋሲል ከነማ አሸናፊነት ተጠናቋል

ሪፖርት | ተጠባቂው ጨዋታ በፋሲል ከነማ አሸናፊነት ተጠናቋል

ዐፄዎቹ በጌታነህ ከበደ ሁለት ጎሎች ፈረሰኞቹን 2ለ1 በማሸነፍ ተከታታይ ሦስተኛ ድል ተቀዳጅተዋል።

ፋሲል ከነማ ወልዋሎን ከረታበት አሰላለፍ የአንድ ተጫዋች ብቻ ለውጥ በማድረግ ኢዮብ ማቲያስን በሸምሰዲን መሀመድ ተክተው ገብተዋል። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል በተመሳሳይ ከሀድያ ሆሳዕና ጋር ያለጎል ጨዋታውን ካጠናቀቀው ስብስባቸው የአንድ ተጫዋች ብቻ ለውጥ በማድረግ ዳግማዊ አርአያን አሳርፈው ፍፁም ጥላውንን በመያዝ ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ፌደራል ዳኛ ሚካኤል ጣዕመ ባስጀመሩት በዚህ ጨዋታ ገና በጨዋታ መጀመርያ አንድ ደቂቃ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊሶች የሰሩትን ጥፋት ተከትሎ ከግራ ጠርዝ ከሳጥን ውጭ የተገኘውን ቅጣት ምት ጌታነህ ከበደ መቶ የግቡ የቀኝ ቋሚ ብረት የመለሰበት ለዐፄዎቹም ሆነ ለጨዋታው ለጎል የቀረበ የመጀመርያ ሙከራ ነበር።

የጨዋታው እንቅስቃሴ ተመጣጣኝ በሆነ መልኩ ቀጥሎ በ13ኛው ደቂቃ ፋሲሎች በቅብብሎች መሐል የሰሩትን ስህተት ተከትሎ ቢንያም ፍቅሬ ያገኘውን ኳስ አክርሮ የመታውን የግቡ ቋሚ ብረት የመለሰበት እንዲሁም ከሁለት ደቂቃ በኋላ በተመሳሳይ የፋሲል ከነማ የኋላ መስመር  ተከላካዮች በራሳቸው ሜዳ የሚሰሩትን ስህተት በድጋሚ ቢንያም ፍቅሬ አግኝቶ የመታውን ግብጠባቂው ፋሲል እንደ ምንም ያዳነበት ፈረሰኞቹ በደቂቃዎች ልዩነት የፈጠሩት ሁለት ወርቃማ ዕድሎች ነበሩ።

በመጀመርያዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች በሁለቱም በኩል ከተፈጠሩት የጎል አጋጣሚዎች በኋላ በተወሰነ መለኩ ጨዋታው እንቅስቃሴ እየተቆራረጠ ዘልቆ 34ኛው ደቂቃ ዐፄዎቹ የመጀመርያ ጎላቸውን አስቆጥረዋል። በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ወደ ማጥቃቱ ክፍል ገብተው አንዋር ወደ መሐል አሾልኮ ለጃቢር የሰጠውን ጃቢር አመቻችቶ ያቀበለውን ጌታነህ ከበደ ከሳጥኑ ውጭ ከጎሉ ፊት ለፊት በመምታት በጥሩ አጨራረስ ወደ ጎልነት ቀይሮታል።

ብዙም ሳይቆይ በ38ኛው ደቂቃ ጌታነህ ከበደ በቀኝ መስመር የተቀበለውን ኳስ የግል ጥረቱን እና ፍጥነቱን እንዲሁም የአጨራረስ ብቃቱን ተጠቅሞ ለራሱም ለቡድኑም ሁለተኛ ጎል አስቆጥሮ ዐፄዎቹን በሁለት ጎል መሪ አድርጓል።

ሁለት ጎል የተቆጠረባቸው በኋላ ፈረሰኞቹ ከፍ ባለ ተነሳሽነት መጫወታቸውን ቀጥለው ለዕረፍት መውጫ ሰከንዶች ሲቀሩት በረከት ወልዴ ከሳጥን ውጭ መቶት ግብጠባቂው ፋሲል ኳሷን ከያዛት በኋላ ጨዋታው ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል።

ከዕረፍት ሲመለሱ ፀጋ ከደር እና ጳውሎስ ከንቲባን በዳግማዊ አርአያ እና አብርሃም ጌታቸውን በማስገባት ፈጣን ቅያሪ ያደረጉት ቅዲስ ጊዮርጊሶች ወደ ጨዋታው ሊመልሳቸው የሚችል ጎል በ52ኛው ደቂቃ አግኝተዋል። በረከት ወልዴ ከግራ መስመር ወደ ውስጥ የላከውን ተቀይሮ የገባው አብርሀም ጌታቸው ኳሷ ተንሸራቶ ወደ ጎልነት ቀይሯታል።

ቅዱስ ጊዮርጊሶች ጎሉን ካስቆጠሩ በኋላ በተሻለ ሁኔታ በተደጋጋሚ ወደ ፊት በመሄድ ጫና ለማሳደር ሲሞክሩ በአንፃሩ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጨዋታውን ለመቆጣጠር ውጤቱ ከእጃቸው እንዳይወጣ በማሰብ የሦስት ተጫዋቾችን ቅያሪ አድርገዋል። በዚህም ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ባይሆንም 62ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው አማኑኤል ገብረሚካኤል ግራ መስመር ይዞ በመግባት ለጌታነህ ከበደ አቀብሎት ጌታነህ በቀላሉ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

በሁለቱም በኩል ተጨማሪ ጎሎች ለማስቆጠር የነበራቸው ጥረት እየተቀዛቀዘ ቢሄድም አንፃራዊነት ወደ ፊት በመሄድ እና ኳሱን በመቆጣጠር ፈረሰኞቹ የተሻሉ ሆነው እየታዮበት ጨዋታው እንቅስቃሴ ወደ ሰባ አምስተኛው ደቂቃ ላይ ደርሷል። በቀሩት ደቂቃዎች ከዕረፍት ከተመለሱ በኋላ በፈረሰኞቹ  የተወሰደባቸውን ብልጫ መልሰው ያገኙት ፋሲል ከነማዎች ጨዋታውን በተገቢው መንገድ በመቆጣጠር በመልሶ ማጥቃት ጫና ፈጥረው 88ኛው ደቂቃ ኪሩቤል ዳኜ ሞክሮ ግብጠባቂው ተመስገን ያዳነበት እንዲሁም በተጨማሪ ደቂቃ አቤል እያዩ ያልተጠቀመበት ብልጫ ለመውሰዳቸው ማሳያ ነበር። የዕለቱ ዳኛ የጨዋታው መጠናቀቂያ ፊሽካ ሲጠበቅ ፈረሰኞቹ አቻ የሚሆኑበትን ዕድል ዳግማዊ አርአያ አግኝቶ ግብጠባቂው ፋሲል ይዞበት ጨዋታው በዐፄዎቹ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።