ሪፖርት | ወልዋሎ ዓ.ዩ እና ኢትዮጵያ መድን ነጥብ ተጋርተዋል

ሪፖርት | ወልዋሎ ዓ.ዩ እና ኢትዮጵያ መድን ነጥብ ተጋርተዋል

የሊጉ ራስ ላይ እና ግርጌ ላይ የሚገኙትን ክለቦች ያገናኘው ጨዋታ 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

በኢዮብ ሰንደቁ

24ኛ ሳምንቱን ባስቆጠረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሜዳ በዋና ዳኛ ሃይማኖት አዳነ መሪነት ምሽት 12 ሰዓት ሲል በተጀመረው የወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ እና የኢትዮጵያ መድን ጨዋታ ወልዋሎዎች ባሳላፍነው ሳምንት በፋሲል ከነማ ከተረቱበት ጨዋታ ይዘውት ከገቡት አሰላለፍ ዳዋ ሆቴሳ እና ሰለሞን ገመቹን ወጥተው ፉዓድ አዚዝ እና ኢሞር ማናፍ ሲገቡ መድኖች ሀዋሳ ከተማን ድል ካደረጉበት አሰላለፍ መሐመድ አበራን በዳዊት አውላቸው በመተካት ጨዋታቸውን ጀምረዋል።

ጨዋታው ገና ከጅማሬው በጎል የታጀበ ነበር። 5ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮጵያ መድኑ ተከላካይ ዋንጫ ቱት በፉዓድ አዚዝ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ፉዓድ ወደ ግብነት በመቀየር ቢጫ ለባሾቹን መሪ ማድረግ ችሏል።

ከግቡ መቆጠር በኋላ በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ መጠነኛ የሆነ እንቅስቃሴን ባስመለከተን ጨዋታ ወልዋሎዎች ፈጣን የሆነ ሽግግርን የማጥቃት ዒላማቸው በማድረግ ሲጫወቱ በተቃራኒው ኢትዮጵያ መድኖች ከራሳቸው የግብ ክልል ኳስ መስርተው በአንድ ሁለት ቅብብል ለማጥቃት ሙከራ ሲያደርጉ 23ኛው ደቂቃ ላይ የወልዋሎው ግብ ጠባቂ ከግብ ክልሉ በትክክል መቶ ያላራቀውን ኳስ ያገኘው በረከት ካሌብ ወደ ግቡ በቀጥታ የመታው ኳስ በተከላካዮች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ቃሲም ራዛቅ ራሱ ላይ ግብ አስቆጥሯል።

ያገኙት ግብ መነቃቃትን የፈጠራላቸው ኢትዮጵያ መድኖች ኳስን በመመስረት እና ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስ ረገድ የተሻሉ ነበሩ። በአጋማሹ መጠናቀቂያ ደቂቃ ላይ በወልዋሎ በኩል ፉዓድ አዚዝ እንዲሁም በኢትዮጵያ መድን በኩል አለን ካይዋ እና ያሬድ ካሳዬ የግብ ሙከራ ማድረግ ቢችሉም ግን ግብ ሳያስመለክቱ አቻ በሆነ ውጤት የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ ራሳቸውን አሻሽለው የቀረቡት ኢትዮጵያ መድኖች የማጥቃት ዒላማቸውን ፈጣን ወደሆነ ሽግግር ቀይረው ሲገቡ በተቃራኒው ወልዋሎዎች ጥንቃቄን ምርጫቸው በማድረግ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ሙከራ ሲያደርጉ ተስተውሏል። 61ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ካሳዬ ከግራ መስመር ያቀበለውን ኳስ አቡበከር ሳኒ አግኝቶ በጥሩ አቋቋም ላይ ለወገኔ ገዛኸኝ ቢሰጠውም ወገኔ የሞከረው ኳስ የግቡን ቋሚ ታኮ ለጥቂት ወጥቶበታል።

70ኛው ደቂቃ ላይ አስመስለህ ወድቀሃል በማለት ግብ አስቆጣሪ ተጫዋቻቸውን በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ ያጡት ወልዋሎዎች በቁጥር ብልጫ ቢወሰድባቸውም ውጤቱን አስጠብቀው ለመውጣት ከፍተኛ የሆነ ትንቅንቅ ማድረግ ችለዋል። በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጥሩ የሆነ እንቅስቃሴን ቢያስመለክተንም ግብ በማግባቱ ረገድ ደካማ የሆነ እንቅስቃሴ ነበር።

በመጨረሻዎቹ አስር ያክል ደቂቃዎች ተጨማሪ ቅያሪዎችን በማድረግ ያገኙትን የቁጥር ብለጫ ለመጠቀም መድኖች በጣም ተጭነው ማጥቃት ቢጀምሩም ግን የወልዋሎዎችን የመከላከል ግንብ መናድ ተስኗቸው ጨዋታው 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲዎችም በዳኝነት ላይ በነበራቸው ቅሬታ ቴክኒካል ክስ አስመዝግበዋል።