ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት እና በዋንጫ ፉክክሩ ለመዝለቅ የሚፋለሙት አዳማ ከተማ እና ወላይታ ድቻ የሚያገናኘው ጨዋታ ረፋድ ላይ ይካሄዳል
አዳማ ከተማ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት በሚያደርገው ፉክክር ወሳኝ የሆነውን ጨዋታ ያደርጋል።
በፕሪምየር ሊጉ ካደረጋቸው 21 ጨዋታዎች 31 ግቦች በማስተናገድ በሊጉ ደካማ የመከላከል ቁጥሮች ያስመዘገበው ቡድኑ የኋላ መስመሩ አስተማማኝ እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ታይቷል። ቡድኑ በ19ኛው እና 20ኛው ሳምንት በተካሄዱ ጨዋታዎች በተከታታይ መረቡን ሳያደፍር በመውጣት ውስን መሻሻሎች ማሳየት ቢችልም በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ስድስት ግቦች በማስተናገድ የመከላከል ድክመቱ አገርሽቶበታል። ከዚህ መነሻነት የቡድኑ አጠቃላይ የመከላከል መዋቅር ችግር በነገው ጨምሮ በቀጣይ መርሐ-ግብሮች ፈቶ መቅረብ የአሰልጣኝ አብዲ ቡሊ ቀዳሚ ስራ መሆን ይገባዋል። የመከላከል ድክመቱ በቀዳሚነት የሚነሳ ችግር ቢሆንም የማጥቃት አጨዋወቱ ውጤታማነትም ሌላው የአዳማ ከተማ ድክመት ነው፤ በነገው ዕለትም ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ላስተናገደው የጦና ንቦቹ ጠንካራ የመከላከል ውቅር የሚመጥን አቀራረብ ማበጀት ይጠበቅባቸዋል።
በሰላሣ ስድስት ነጥቦች 3ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት እና በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኙት የጦና ንቦቹ በዋንጫ ፉክክሩ ለመዝለቅ በሚያደርጉት ጉዞ ነገ አዳማ ከተማን ይገጥማሉ።
ቀስ በቀስ እየተሻሻለ በአሁኑ ወቅት በላይኛው ፉክክር ውስጥ የሚገኘው ወላይታ ድቻ የአራት ተከታታይ ድሎች ጉዞውን ማስቀጠል ከምንም በላይ አስፈላጊው ነው። ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች ሁለት ነጥቦች ብቻ የጣለው እና በተጠቀሱት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ያስተናገደው የጦና ንቦቹ ስብስብ ከውስን የግብ ማስቆጠር ድክመቱ በስተቀር በአስደናቂ ወቅታዊ ብቃት ላይ ይገኛል። በቅርብ ሳምንታት ዝቅተኛ ግብ ያስተናገደው ቡድኑ በጥንቃቄ እንደማይታማ ቁጥሮች በራሳቸው ምስክር ናቸው፤ ሆኖም ከድሎቹ ባሻገር በሚፈለገው መጠን ግቦችን እያስቆጠረ አለመሆኑ ከነገው ጨዋታ በፊት መሻሻል የሚገባው ጉዳይ ነው።
በጦና ንቦቹ በኩል ባለፈው ሳምንት በህመም ምክንያት ከጨዋታ ውጭ የነበረው ተከላካዩ አዛርያስ አቤል ከህመሙ አገግሞ መመለሱ ሲሰማ የተቀሩት የቡድኑ ተጫዋቾችም ለነገው ጨዋታ ዝግጁ መሆናቸው ታውቋል። በአዳማ ከተማ በኩል ግብ ጠባቂው ዳግም ተፈራ ከረዥም ጊዜ ጉዳት ሲመለስ የቻላቸው መንበሩ መሰለፍ ግን አጠራጣሪ ነው።
ቡድኖቹ 21 ጊዜ ተገናኝተው ወላይታ ድቻ 9 በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን አዳማ ከተማ 7 ጨዋታ አሸንፏል። ቀሪው 5 ጨዋታ ደግሞ አቻ ተጠናቋል። ወላይታ ድቻ 24፣ አዳማ 20 ግቦች አስቆጥረዋል። (የተሰረዘው የ2012 የውድድር ዘመን አልተካተተም