ነብሮቹ እና ብርቱካናማዎቹ የሚፋለሙበት ጨዋታ የዕለቱ ሁለተኛ መርሐግብር ነው።
በቅርብ ጨዋታዎች ላይ መጠነኛ የውጤት መጥፋት የገጠማቸው ሆዲያ ሆሳዕናዎች በሰላሣ ሦስት ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
ቅዱስ ጊዮርጊስን ካሸነፉበት ጨዋታ በኋላ በተካሄዱ አራት ጨዋታዎች ከድል ጋር የተራራቁት ነብሮቹ ባለፉት ሳምንታት ባስመዘገቧቸው ውጤቶች ከነበሩበት የመሪዎች ጎራ እንዲያሽቆለቁሉ ሆኗል። የፊት መስመሩ መዳከም ደግሞ ለዚህ እንደምክንያት ከሚጠቀሱት ነጥቦች አንዱ ነው፤ ቡድኑ ከአዞዎቹ ጋር አቻ ከተለያየበት እና ሦስት ግቦች ካስቆጠረበት ጨዋታ በኋላ በተከናወኑ ስድስት መርሐግብሮች ላይ ሁለት ግቦች ብቻ ማስቆጠሩም የዚህ ማሳያ ነው። በነገው ዕለት ደግሞ በተለይም በመጨረሻው መርሐግብር ጥሩ እንቅስቃሴ አድርጎ አዳማ ከተማን ሦስት ለአንድ ካሸነፈው ድሬዳዋ ከተማ እንደመግጠሙም በርካታ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ቢቸገር እንኳን ከጥቁት አጋጣሚዎች ውጤት ቀያሪ ግቦች ከአጥቂዎቹ ይፈለጋሉ።
በመጨረሻው መርሐግብር ወሳኝ ድል አስመዝግቦ ነጥቡን ሀያ አምስት ያደረሰው ድሬዳዋ ከተማ ከአስራ አንድ የጨዋታ ሳምንታት ጥበቃ በኋላ ያገኘውን ድል ለማስቀጠል ሀድያ ሆሳዕናን ይገጥማል።
ከስጋት ቀጠናው ለመውጣት በሚያደርገው ጉዞ ወሳኝ እና አስፈላጊ ድል ማግኘት የሚጠበቅበት የብርቱካናማዎቹ ስብስብ የግብ ማስቆጠር ችግሩን መፍታቱ በቀጣይ መርሐ-ግብሮች የተሻለ ግምት እንዲሰጠው ያደርጋል። በርግጥ ቡድኑ በነገው ዕለት በሊጉ ዝቅተኛ የግብ መጠን በማስተናገድ በ4ኛ ደረጃ የተቀመጠውን ሀድያ ሆሳዕና እንደመግጠሙ ከባድ ፍልሚያ ይጠብቀዋል ተብሎ የሚገመት ቢሆንም በመጨረሻው ጨዋታ ያሳየው የማጥቃት እንቅስቃሴ ግን ተስፋ ሰጪ ነው። ለአራት ተከታታይ ጨዋታዎች ኳስና መረብ ሳያገናኙ ከዘለቁ በኋላ በ11 መርሐግብሮች ካስቆጠሩት የግብ መጠን የሚስተካከል ግብ በአንድ ጨዋታ ያስቆጠሩት ብርቱካናማዎቹ በማጥቃቱ ረገድ ያሳዩት መሻሻል ማስቀጠል የሚችሉ ከሆነ ከነገው ጨዋታ አንዳች ነገር ይዘው እንዲወጡ ያግዛቸዋል።
በድሬዳዋ ከተማ በኩል መሐመድኑር ናስር በጉዳት ሔኖክ ሀሰን ደግሞ በቅጣት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ ናቸው። በሀድያ ሆሳዕና በኩል አሁንም የረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ የሚገኙት መለሰ ሚሻሞ ፣ በረከት ወንድሙ ፣ ጫላ ተሺታ በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጭ ናቸው፤ በተጨማሪም በባለፈው ጨዋታ ያልነበረው አንበሉ ሄኖክ አርፊጮ በቀጣይ ለሦስት ሳምንት ከሜዳ እንደሚርቅ ተረጋግጧል። ብሩክ ማርቆስን በአምስት ቢጫ በነገው ጨዋታ የሚያጡት ነብሮቹ የተቀረውን ስብስባቸውን ይዘው ወደ ሜዳ እንደሚገቡ አውቀናል።
ቡድኖቹ በሊጉ 11 ጊዜ ሲገናኙ ነብሮቹ 5 ስያሸንፉ ብርቱካናማዎቹ 4 ጊዜ ድል አድርገው
2 ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል። 29 ግቦች በተስተናገዱበት ግንኙነት ሀድያ ሆሳዕና 16 ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ 13 ጎሎች አስቆጥረዋል