በዕለቱ ሁለተኛ መርሐግብር ሀዲያ ሆሳዕና እና ድሬዳዋ ከተማ በሁለቱ አጋማሾች በተቆጠሩ ግቦች አንድ አቻ ተለያይተዋል።
ያለፉትን አራት ጨዋታዎች ማሸነፍ ያልቻሉት ሀድያ ሆሳዕናዎች ከፈረሰኞቹ ጋር ያለጎል ካጠናቀቁው ስብስብ የሁለት ተጫዋቾችን ለውጥ ሲያደርጉ ብሩክ ማርቆስ እና ብሩክ በየነ በከማል ሀጂ እና በየነ ባንጃን ተተክተዋል ፤ ከአስራ አንድ ጨዋታ በኋላ አዳማ ከተማን 3-1 በማሸነፍ ከድል ጋር የታረቁት ድሬዳዋ ከተማዎች በተመሳሳይ ሁለት ተጫዋቾች ሲለውጡ በዚህም ሄኖክ ሀሰን እና መሱዑድ መሐመድ አሳርፈው አቡበከር ሻሚል እና ሙኸዲን ሙሳን በመጀመርያው አስተላለፍ አካተዋል።
ፌደራል ዳኛ ሙልቀን ያረጋል በመሩት ይህ ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክርን በማስመልከት የጀመረ ሲሆን የግብ ሙከራ ለማስተናገድ ግን ዘለግ ያሉ ደቂቃዎች ፈጅቶበታል።
በእንቅስቃሴ ደረጃም ሀዲያ ሆሳዕናዎች ከፊት የሚገኙ አጥቂዎቻቸውን ታሳቢ ያደረጉ ወደ መስመር የሚጣሉ ፈጣን ሽግግሮች ለማድረግ ሲጥሩ ድሬዳዋ ከተማዎች በበኩላቸው በቅብብሎሽ ክፍት ሜዳ የመፈለግ እንቅስቃሴ አድርገዋል።
ጨዋታውም የመጀመሪያ ሙከራ በ24ኛው ደቂቃ ተመስገን ብርሃኑ ያስጀመረውን ኳስ ኢዮብ ተቀብሎ ወደ ውስጥ የመታውን ግብጠባቂው አላዛር መልሶበታል።
በተሻለ ብልጫ የነበራቸው ነብሮቹ 36ኛው ደቂቃ የድሬዳዋው ተከላካይ ጀሚል ያዕቆብ ለቡድን አጋሩ ኳሱን ወደ ኋላ አቀብላለው ብሎ የተሳሳተውን ኳስ እዮብ ዓለማየሁ አግኝቶ ኳሱን ወደ ፊት በመግፋት ከግራ ጠርዝ ወደ ውስጥ የላከውን ሰመረ ሃፍታይ ወደ ጎል የመታውን ግብ ጠባቂው አላዛር በጥሩ ቅልጥፍና ያዳነው ለሀድያ ሆሳዕናዎች እጅግ ለጎል የቀረበ ሙከራ ነበር።
በዚህ ሂደት የቀጠሉት ሀድያ ሆሳዕናዎች የአጋማሹ መገባደጃ ጭማሪ ደቂቃ ላይ የመጀመርያ ጎላቸውን አግኝተዋል ፤ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ሽግግር ከሰመረ ሃፍታይ የተነሳው ኳስ ግብ ጠባቂው አላዛር ከቦታው ለቆ ኳሷን ለማዳን ሲተፋው ተመስገን ብርሃኑ አግኝቶ መረቡ ላይ አሳርፎት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሩ ድሬዳዋ ከተማ ወደ ጨዋታው ለመግባት ብዙም ሳይቆዩ በ56ኛው ደቂቃ ላይ አቻ መሆን ችለዋል። አስራት ቱንጆ ለማሻመት በሚመስል መልኩ ወደ ጎል የላካውን ቀላል ኳስ ግብ ጠባቂው ሚካኤል ሳማኪ ኳሱን በመትፋት የሰራውን ስህተት ተጠቅሞ አቤል አሰበ ኳሱን ወደ ጎልነት ቀይሮታል።
የአቻነቱ ጎል ከተስተናገደ በኋላ የጨዋታው ረዘም ያሉ ደቂቃዎች በሁለቱም በኩል ተመጣጣኝ የሆነ ፉክክር እያስመለከተን ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ቢደርሱም ከአፈፃፀም አኳያ ደካማ በመሆናቸው እጅግ የጠራ የጎል ሙከራ መፍጠር አቅቷቸዋል።
ሆኖም የጨዋታውን የመጨረሻ አስር ደቂቃዎች በተወሰነ መልኩ ነብሮቹ ጫና ፈጥረው ጎል ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም የድሬዳዋን የመከላከል አጥርን ሰብረው መግባት አልቻሉም። ጨዋታውም አንድ አቻ በሆነ ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል።