ወልዋሎ ከአሠልጣኙ ጋር ተለያይቷል

ወልዋሎ ከአሠልጣኙ ጋር ተለያይቷል

በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ የተቀመጠው ወልዋሎ ዓ/ዩ ከአሠልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ጋር መለያየቱ ተረጋግጧል።

ከሰሜኑ የሀገራችን ጦርነት በኋላ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ዳግም የተቀላቀለው ወልዋሎ ዓ/ዩ በአሠልጣኝ አሸናፊ በቀለ እየተመራ የውድድር ዓመቱን ቢጀምርም የውጤት ቀውስ ገጥሞት ከአሠልጣኙ ጋር የነበረው ጋብቻ ከ95 ቀናት የዘለለ አልነበረም። ከዛም አሠልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያምን በመሾም ከ7ኛ ሳምንት ጀምሮ ውድድሩን ሲያደርግ ሰንብቷል።

በ22 የሊጉ ጨዋታዎች ከ10 ነጥብ በላይ ማስመዝገብ ያልቻለው ወልዋሎ በትናንትናው ዕለት ከኢትዮጵያ መድን ጋር ነጥብ ከተጋራ በኋላ የክለቡ የቦርድ አመራር ዛሬ ስብሰባ ተቀምጧል። በዚህም የዝግጅት ክፍላችን ሶከር ኢትዮጵያ ከውስጥ ምንጮች ባገኘችው መረጃ ክለቡ አሠልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያምን ከቦታው ማንሳቱ ታውቋል። በቀጣይ ክለቡ አዲስ አሠልጣኝ እስኪሾም ድረስም በምክትል አሠልጣኞቹ እንደሚመራ ለማወቅ ተችሏል።