ሪፖርት | መቻል ከዘጠኝ ሳምንታት በኋላ አሸንፏል

ሪፖርት | መቻል ከዘጠኝ ሳምንታት በኋላ አሸንፏል

መቻሎች መቐለ 70 እንደርታን 1-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ከዘጠኝ ሳምንታት በኋላ ከናፈቃቸው ድል ጋር ታርቀዋል።

በኢዮብ ሰንደቁ

መቻል እና መቐለ 70 እንደርታን ያገናኘው የምሽቱ ጨዋታ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሜዳ በኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ መሪነት ሲጀመር መቻሎች ነስረዲን ሀይሉን፣ ምንይሉ ወንድሙ እና ዮሴፍ ታረቀኝን በማሳረፍ በምትካቸው ግሩም ሀጎስ፣ አማኑኤል ዮሐንስን እና ዳዊት ማሞን በማስገባት ሲጀምሩ በመቐለ 70 እንደርታ በኩል ሰለሞን ሀብቴ እና ሙሉጌታ ወ/ጊዮርጊስ በማስወጣት መድሃኔ ብርሃኔ እና ኢማኑኤል ሳባንን በማስገባት ጨዋታቸውን ጀምረዋል።

በሁለቱም ቡድኖች በኩል የመጀመሪያዎቹን ደቂቃዎች ጥሩ እንቅስቃሴን ያስመለከተን ሲሆን 10ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያውን ሙከራ መቐለዎች በብሩክ ሙሉጌታ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ በተመታ ኳስ ሙከራ ማድረግ የቻሉ ሲሆን ግብ ጠባቂው አልዌንዚ ናፊያን ግብ ከመሆን ታድጓታል።

በጨዋታው ከኳስ ጋር ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረጉ ረገድ መቻሎች የተሻሉ ቢሆኑም በሙከራ ረገድ መቐለዎች የተሻሉ ነበሩ። የማጥቃት መነሻቸውን በመስመር በኩል በማድረግ 15ኛው ደቂቃ ላይ ሔኖክ አዱኛ ከቀኝ መስመር የመታው ኳስ ግብጠባቂው መልሶበታል። በድጋሚ 24ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ያገኙትን ኳስ ከቀኝ መስመር ያሬድ ከበደ በነፃ አቋቋም ላይ ለሚገኘው ቦና አሊ ቢያቀብለውም ግብጠባቂው ኳሷን ጨርፎ ወደ ውጭ አስወጥቶቷል።

በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴን የሚያደርጉት እና ኳስን በአንድ ሁለት ቅብብሎሽ መስርተው በመጫወት መሃል ላይ ብልጫ በመውሰድ ግብ ለማግኘት የሚሞክሩት መቻሎች የመጀመሪያ ሙከራቸውን 40ኛው ደቂቃ ላይ ማድረግ ችለዋል። አቤል ነጋሽ በሜዳው በግራ ክፍል አክርሮ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ሶፎንያስ መልሶበታል። ይህንንም ተከትሎ ያለምንም ግብ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ላይ በከፍተኛ ግብ የማግባት ፍላጎት ወደ ሜዳ የተመለሱት መቻሎች በመጀመሪያው አጋማሽ የነበራቸውን የግብ ሙከራ በማስተካከል የመጀመሪያ ግባቸውን ማግኘት ችለዋል።

52ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ አንድ ሁለት ቅብብል ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል ይዘውት የገቡትን ኳስ አለምብርሃን ይግዛው ከቀኝ መስመር ያቀበለውን ኳስ ሽመልስ በቀለ የግል ችሎታውን በመጠቀም ግሩም በሆነ አጨራረስ ግብ በማስቆጠር መቻልን መሪ ማድረግ ችሏል።



በሁለቱም ቡድኖች መካከል ፈጣን በሆነ ሽግግር ወደ 3ኛዉ የሜዳ ክፍል መድረስ የቻሉ ሲሆን በመጠኑ መቐለ 70 እንደርታዎች የተሻለ መንቀሳቀስ ችለዋል። ነገር ግን ረዘም ያሉ ደቂቃዎችን ያለ ሙከራ ያስመለከተን ጨዋታ 85ኛው ደቂቃ ላይ መቻሎች በኢዲሱ ፈራሚያቸው ኮሊን ኮፊ አማካኝነት ለግብ የቀረበን ሙከራ ማድረግ ችለዋል። ብዙም የግብ ሙከራዎችን ባላስመለከተን ጨዋታ መቻል መቐለ 70 እንደርታን 1-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።