ስሑል ሽረ እና ሲዳማ ቡና የሚያገናኘው ለሁለቱም ቡድኖች ወሳኝ የሆነው ጨዋታ የ24ኛው ሳምንት መገባደጃ መርሐ-ግብር ነው።
በአስራ ስድስት ነጥቦች 17ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ስሑል ሽረዎች በመጨረሻው ጨዋታ ከተከታታይ ሽንፈቶች መልስ ያሳኩት አንድ ነጥብ ወደ ድል በማሳደግ በወራጅ ቀጠናው ካሉ ክለቦች ያላቸው የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ ወደ ሜዳ ይገባሉ።
ጠንካራው ባህርዳር ከተማ በገጠመበት የመጨረሻው ሳምንት ጨዋታ ነጥብ የተጋራው ስሑል ሽረ ቢያንስ ከበላዩ ካሉት ቡድኖች ያለውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ እና ላለመውረድ በሚደርገው ፍልሚያ ውስጥ ተስፋን የሚያልምበት ጨዋታ ያደርጋል። በመጨረሻው ጨዋታ ከተከታታይ ሦስት ሽንፈቶች መልስ የሁለተኛውን ዙር የመጀመርያ ነጥቡን ያስመዘገበው ቡድኑ በዕለቱ በብዙ ረገድ የተሻሻለ ብቃት ማሳየቱ በነገው ጨዋታ ከሌላው ጊዜ የተሻለ ግምት እንዲሰጠው ያስገድዳል። በተለይም ጠንካራ ቡድን በገጠመበት ጨዋታ ላይ ከሦስት መርሐ-ግብሮች በኋላ ግብ ሳያስተናግድ መውጣት መቻሉ ጠንካራ ጎኑ ነበር።
ሆኖም ባለፉት አራት ጨዋታዎች ኳስና መረብ ማገናኘት የተሳነው እና በመጨረሻዎቹ አስር ጨዋታዎች ሦስት ግቦች ብቻ ያስቆጠረው የማጥቃት አጨዋወቱን ማስተካከል በቀጣይ የሚጠብቀው ትልቁ ስራ ነው። ባህርዳር ከተማን በገጠሙበት ጨዋታ በርከት ያሉ የተጫዋች እንዲሁም የአደራደር ለውጥ ያደረጉት አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት በነገው ጨዋታ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ያሳየው የመከላከል አደረጃጀታቸው ጥንካሬ ከማስቀጠል ባለፈ ትልቁ የቡድናቸው ድክመት የሆነው የግብ ማስቆጠር ችግር መቅረፍ ግድ ይላቸዋል።
በሀያ ስድስት ነጥቦች በ13ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሲዳማ ቡናዎች ካሉበት የስጋት ቀጠና ለመራቅ በወራጅ ቀጠናው ከተቀመጠው ስሑል ሽረ ይፋለማሉ።
በመጨረሻው ሳምንት ከአራት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኋላ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሽንፈት የገጠማቸው ሲዳማ ቡናዎች በጨዋታው ከሌላው ጊዜ አንፃር የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረግ ቢችሉም በጨዋታው መገባደኛ ደቂቃዎች በተቆጠረባቸው ግብ ሽንፈት ማስተናገዳቸው ተከትሎ ከአምስት ሽንፈት አልባ ጨዋታዎች በኋላ ነጥብ ሳያስመዘግቡ ወጥተዋል። ሲዳማ ቡናዎች በደጋፊያቸው ፊት ባደረጉት የመጀመርያ ጨዋታ በብዙ ረገድ ተሻሽለው ቢቀርቡም ጫና ፈጥረው በተጫወቱባቸው ደቂቃዎች ያገኟቸውን የግብ ዕድሎች በመጠቀም ረገድ የነበረባቸውን ድክመቶች ዋጋ አስከፍሏቸዋል፤ ከባለፉት መርሐ-ግብሮች አንፃር ሲታይ በመጨረሻው ጨዋታ በማጥቃቱ ረገድ ጉልህ መሻሻል ያሳየው ቡድኑ በቀጣይ መርሐ-ግብሮች በግብ ፊት ያለበትን ውስንነት መቅረፍ ይኖርበታል። በነገው ዕለትም በመጨረሻው መርሐ-ግብር የባህርዳር ከተማን የማጥቃት አጨዋወት በማምከን ረገድ ውጤታማ ስራ ሰርቶ ወደ ነገው ጨዋታ የሚቀርበው ስሑል ሽረ እንደመግጠማቸው በመጨረሻ ጨዋታ ላይ የታዩትን የአፈፃፀም ድክመቶች ማረም ይጠበቅባቸዋል።
ከወራጅ ቀጠናው አፋፍ ካለው ቡድን በአንድ ነጥብ እና ደረጃ ብቻ ከፍ ብሎ የሚገኘው ቡድኑ ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ ከድል ጋር በመታረቅ ከአስጊው ቀጠና በትንሹም ቢሆን ፈቅ ለማለት ጠንካራ ፉክክር እንደሚያደርግ ይገመታል።
ስሑል ሽረዎች በነገው ጨዋታ በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም፤ በሲዳማ ቡና በኩልም አንተነህ ተስፋዬ በጉዳት ካለመኖሩ በቀር ሁሉም የቡድኑ አባላት ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው።
ቡድኖቹ በሊጉ ሦስት ጊዜ ተገናኝተው ሲዳማ ሁለቱን ሲያሸንፍ በአንዱ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል። ሲዳማ አምስት ሲያስቆጥር ሽረ ደግሞ ሦስት ማስቆጠር ችሏል (የተሰረዙትን የ2012 ሁለት ጨዋታዎች አያካትትም)።