ሪፖርት | ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ሀዋሳ ከተማ አቻ ተለያይተዋል

ሪፖርት | ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ሀዋሳ ከተማ አቻ ተለያይተዋል

በሁለቱም አጋማሾች 18ኛ ደቂቃ ላይ በተቆጠሩ ግቦች ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ሀዋሳ ከተማ 1-1 ተለያይተዋል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ በአርባምንጭ ከተማ 2-0 ከተሸነፉበት አሰላለፍ  ጌቱ ባፋ፣ ጋሻው ክንዴ፣ አበባየሁ ዮሐንስ እና ፍቃዱ አለሙን አሳርፈው ሚኪያስ ካሳሁን፣ አሸናፊ ጥሩነህ፣ ኢዮብ ገብረማርያም እና ሄኖክ ገብረህይወትን ተክተው ሲገቡ ኃይቆቹ በአንፃሩ በኢትዮጵያ መድን 2-1 ከተሸነፉበት ስብስብ ብሩክ ታደሰ፣ አብዱባሲጥ ከማል እና ታፈሰ ሰለሞንን በዳንኤል አበራ፣ አቤኔዘር ዮሐንስ እና ያሬድ ብሩክ ተክተው ገብተዋል።

በዋና ዳኛ ቢኒያም ወርቅአገኘው መሪነት በተጀመረው ጨዋታ በጣም የቀዝቀዝ ያለ እንቅስቃሴ እያስመለከተን ጅማሮውን ቢያደርግም  የጨዋታውን የመጀመርያ ሙከራም ሆነ ጎል በ18ኛው ደቂቃ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች አስቆጥረዋል። በማጥቃት ሽግግር በመግባት ከግራ መስመር ጠርዝ ላይ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ በጥሩ መንገድ ያሻገረውን አቤል ሀብታሙ በግንባሩ በመግጨት ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

የተቀዛቀዘውን የጨዋታ መንፈስ በተቆጠረችው አንድ ጎል ተነቃቅቶ ይቀጥላል ቢባልም በሁለቱም በኩል ስኬታማ ባልሆኑ ቅብብሎች ምክንያት ጨዋታው እየተቆራረጠ ቢቀጥልም በአንፃራዊነት ሀዋሳ ከተማዎች ወደ ፊት በመሄድ የተሻሉ ነበሩ። በ38ኛው ደቂቃም ኃይቆቹ ከ18 ሜትር ርቀት ላይ ያገኙትን ቅጣት ምት ያሬድ ብሩክ የመታውን የግቡ አግዳሚ የመለሰበት ሀዋሳዎች ወደ ጨዋታው ሊገቡበት የሚችሉበት ጥሩ አጋጣሚ ነበር። ኢትዮ ኤሌትሪኮች ጎል ካስቆጠሩ በኋላ የተወሰደባቸውን ብልጫ ለመውሰድ የሚያደርጉት ጥረት ዕምብዛም ያልነበረ ሲሆን በአንፃሩ ሀዋሳዎች የወሰዱትን የበላይነት ወደ ጎልነት ለመቀየር ጥረት ቢያደርጉም ስኬታማ ሳይሆኑ አጋማሹ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ በአጋማሹ የወሰዱትን ብልጫ አጠናክረው የቀጠሉት ኃይቆቹ ወደ ጎልነት የሚቀየር ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ በማድረጉ ረገድ የነበረ ድክመት በኋላ ላይ 60ኛው ደቂቃ በተገኘ የፍፁም ቅጣት ምት ጎል ወደ ጨዋታው ተመልሰዋል። የኢትዮ ኤሌክትሪክ ተከላካዮች የሰሩትን ጥፋት ተከትሎ ከአስራ ስድስት ከሀምሳ ውጭ የተሰጠውን ቅጣት ምት ዓሊ ሱሌይማን ሲመታው ሽመክት ጉግሳ በእጁ ኳሱን ነክተሀል በሚል የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ዓሊ ወደ ጎልነት ቀይሮት ቡድኑን አቻ አድርጓል።

አስቀድመው በራሳቸው የሜዳ ክፍል በቁጥር በዝተው ይከላከሉበት ከነበረው የጨዋታ መንገድ ቀይረው ወደ ማጥቃት እንቅስቃሴ በመግባት የጎል ዕድሎችን መፍጠር የጀመሩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በ73ኛው ደቂቃ ሄኖክ ገብረህይወት በግል ጥረቱ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ሳጥን ውስጥ በመግባት ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ሰኢድ በጥሩ ንቃት ያዳነበት ተጠቃሽ ሙከራ ነበር።

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በሁለቱም በኩል ካሉበት የውጤት ማጣት አንፃር ያለችውንም አንድ ነጥብ አስጠብቀው ለመውጣት የጥንቃቄ  አጨዋወት መምረጣቸውን ተከትሎ ይህ ነው ተብሎ የሚጠቀስ የጠራ ሙከራ ሳንመለከት ጨዋታው አንድ አቻ በሆነ ውጤት ተገባዷል።