ሪፖርት | ሲዳማ ቡና ስሑል ሽረን አሸንፏል

ሪፖርት | ሲዳማ ቡና ስሑል ሽረን አሸንፏል

ሲዳማ ቡናዎች ከ አምስት ተከታታይ ጨዋታ በኋላ ስሑል ሽረን 1-0 በማሸነፍ ወደ ድል ተመልሰዋል።

በኢዮብ ሰንደቁ

24ኛ ሳምንቱን ባስቆጠረው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሜዳ ምሽት 12 ሰዓት ሲል የተጀመረው የስሑል ሽረ  እና የሲዳማ ቡና ጨዋታ ስሑል ሽረዎች ከባህር ዳር ከተማ ጋር ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ ይዘውት ከገቡት አሰላለፍ  ኤቢሳ ከድር እና ሙሀመድ አብዱል ላጢፍን በማሳረፍ በምትካቸው ክፍሎም ገ/ሂወት እና አላዛር ሽመልስን ሲያስገቡ በሲዳማ ቡና በኩል ደግ  በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከተሸነፉበት አሰላለፍ ያሬድ ባየህን በጊት ጋትኩት በመተካት ጨዋታቸውን ጀምረዋል።

ሁለቱም ቡድኖች ከጨዋታው ጅማሬ አንስቶ ጥሩ የሆነን የኳስ እንቅስቃሴን ያስመለከቱን ሲሆን ፈጣን በሆነ ሽግግር በሶስተኛው የሜዳ ክፍል በመገኘት ግብ ለማግኘት ሲሞክሩ ተስተውሏል። በግብ መኩራ ረገድ የተሻሉ የነበሩ ሲዳማ ቡናዎች ሲሆኑ ብርሃኑ በቀለ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ አክርሮ በመታው እና በቅጣት ምት ኳስ ሙከራ ማድረግ ችለዋል።

30ኛው ደቂቃ ላይ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን ከመሃሉ የሜዳ ክፍል ይዞት የገባውን ኳስ ከሀብታሙ ታደሰ ጋር በጥሩ አንድ ሁለት ቅብብል ወደ ሳጥን በመግባት ያገኘውን ኳስ ራሱ ፍቅረየሱስ ወደ ግብነት በመቀየር ሲዳማ ቡናን መሪ ማድረግ ችሏል።

35ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ታደሰ ከቀኝ መስመር ከሬድዋን ናስር የተቀበለውን ኳስ ድንቅ በሆነ ችሎታው ተከላካይ እና በረኛን በማለፍ ከግቡ በግራ ቋሚ ጎንን በመሆን የሞከረው ቄንጠኛ ኳስ የግቡን ቋሚ ገጭታ በስሑል ሽረ ተከላካዮች ወጥታለች። ከግቡ መቆጠር በኋላ የመጨረሻዎቹን ደቂቃዎች ስሑል ሽረዎች መንቀሳቀስ ቢችሉም የውጤት ለውጥ ሳይኖር 1-0 በሆነ ውጤት የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ላይ በሁለቱም ቡድኖች በኩል በመቀዛቀዝ ጨዋታቸውን የጀመሩ ሲሆን በአንጻራዊነት ሲዳማ ቡናዎች የተሻለ መንቀሳቀስ ሲችሉ 68ኛው ደቂቃ ላይ ከሲዳማ ቡናው ሀብታሙ ታደሰ ሙከራ በስተቀር ምንም አይነት ይህ ነው የሚባል ሙከራ ሳያስመለክተን ረዘም ያሉ ደቂቃዎችን አስቆጥሯል።

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ግለት እና ሽኩቻ በበዛበት ጨዋታ ሲዳማ ቡናዎች ነጥባቸውን አስጠብቀው ለመውጣት በተቃራኒው ደግሞ ሽረዎች ነጥብ ተጋርተው ለመውጣት ከፍተኛ ትንቅንቅን ያስመለከተን ሲሆን በቁጥር በዝተው ጫና መፍጠር የቻሉት ሽረዎች 90+3′ ግብ ማስቆጠር ቢችሉም የእለቱ የመስመር ዳኛ ከጨዋታ ውጭ በሚል ግቡን የሻረው ሲሆን በዚህም የተነሳ ለጥቂት ደቂቃዎች ውዝግብ ቢያስነሳም ጨዋታው ቀጥሎ ጨዋታው በሲዳማ ቡናዎች 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።