በሁለት ነጥብ የሚበላለጡት አዞዎቹ እና ሀምራዊ ለባሾቹ ደረጃቸውን ለማሻሻል የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
ኢትዮ ኤሌክትሪክን ሁለት ለባዶ አሸንፈው ነጥባቸው ሰላሣ ሦስት በማድረስ ለነገው ወሳኝ ጨዋታ የሚቀርቡት አርባምንጫ ከተማዎች ደረጃቸውን ለማሻሻል የቅርብ ተፎካካርያቸውን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይገጥማሉ።
በአሰልጣኝ በረከት ደሙ ስር ውጤታማ ጊዜ በማሳለፍ ላይ የሚገኙት አዞዎቹ ውድድሩ በአህጉራዊ ጨዋታዎች ከመቋረጡ በፊት በመቐለ 70 እንደርታ ከደረሰባቸው ሽንፈት በማገገም ዳግም ወደ ድል መንገድ ተመልሰዋል። በሊጉ ክስተት የሆነ፣ ወጥነት ያለው ብቃት በማሳየት ላይ ከሚገኙ ክለቦች ውስጥ የሚጠቀሰው የአዞዎቹ ስብስብ በተለይም በማጥቃቱ ረገድ ያላቸው ጥንካሬ በሰንጠረዡ የላይኛው ክፍል እንዲፎካከሩ አስችሏቸዋል። በሊጉ ከፍተኛ የግብ መጠን ካስመዘገበው መሪው መድን በሁለት ግቦች ብቻ ያነሰ ማስቆጠር የቻለው ቡድኑ ከነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ይዞ የሚወጣ ከሆነ ሁለት ደረጃዎች የማሻሻል ዕድል በእጁ ይገኛል።
አዞዎቹ በመጀመርያው ዙር የመጨረሻ ጨዋታዎች የታዩባቸው የመከላከል ድክመቶች በሂደት መቅረፍ መቻላቸውም ሌላው በቡድኑ የሚጠቀስ አወንታዊ ነጥብ ነው፤ ቡድኑ ከ 17ኛ እስከ 19ኛ ሳምንት በተከናወኑ ሦስት መርሐ-ግብሮች ሰባት ግቦች ቢያስተናግድም ከዛ በኋላ በተከናወኑ አራት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ ማስተናገዱም የመሻሻሉ አንድ ማሳያ ነው።
ሰላሣ አንድ ነጥቦች ሰብስበው በ9ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች የጀመሩት የሽቅብ ጉዞ ለማስቀጠል በሁለት ነጥቦች ልቀው ከተቀመጡት አዞዎቹ ይፋለማሉ።
ከቀዝቃዛው አጀማመር አገግመው በጥሩ ወቅታዊ ብቃት የሚገኙት ሀምራዊ ለባሾቹ በሂደት ወደ ትክክለኛው ቅርፅ የመጡ ይመስላል። ከሊጉ መጀመር አንስቶ ጨዋታን በመቆጣጠር ይሁን የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በመውሰድ ረገድ የማይታማው የአሰልጣኝ በፀሎት ቡድን በቅርብ ሳምንታት ግን በማጥቃቱም ረገድ ጉልህ መሻሻል ማሳየቱን ተከትሎ ወደ ውጤታማነት መልሶታል። ቡድኑ በመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው አስራ ሁለት ነጥብ ዘጠኙን ማሳካቱም በውጤት ደረጃ መሻሻሉን ማሳያ ነው።
ንግድ ባንክ በመጨረሻው መርሐ-ግብር ከሌላ ጊዜ አንፃር ሲታይ ምንም እንኳን ጨዋታውን ለመቆጣጠር የሄደበት ርቀት እምብዛም ቢሆንም ጥሩ ባልተንቀሳቀሰበት ጨዋታም ጭምር ነጥብ ይዞ መውጣት መጀመሩ የቡድኑ የአሸናፊነት መንፈስ ያለበት ደረጃ ማሳያ ነው። በነገው ዕለት በሁለት ነጥቦች ልቆ ከተቀመጠው እና በጥሩ ብቃት ያለውን አርባምንጭ ከተማ በሚገጥሙበት ጨዋታም በቅርብ ሳምንታት ያሳዩትን መነቃቃት ለማስቀጠል እና ድል አድርገው በሊጉ ሠንጠረዡ ሦስት ደረጃዎች ለማሻሻል እያለው ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይታመናል።
33 እና 31 ነጥቦች የሰበሰቡት ሁለቱ ቡድኖች ወደ ሰንጠረዡ ጫፍ የሚያስጠጋቸውን ዕድል ከዚህ ጨዋታ የሚያገኙ መሆኑ ሲታሰብ ፉክክሩ በጉጉት እንዲጠበቅ ያደርገዋል፤ ጨዋታውም በግቦች የታጀበ የሚሆንበት ዕድል የሰፋ ነው።
በአርባምንጭ ከተማ በኩል አበበ ጥላሁን አሁንም በጉዳት ምክንያት የነገው ጨዋታ ያመልጠዋል፤ እንዳልካቸው መስፍንም ባጋጠመው ጉዳት የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ነው። በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ቢንያም ካሳሁን ቅጣቱን ጨርሶ ሲመለስ አዲስ ግደይ በጉዳት ምክንያት የነገው ጨዋታ የሚያመልጠው ይሆናል። ሌሎቹ የቡድኑ አባላት ለነገው ጨዋታ ተሟልተው ይቀርባሉ።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ በአጠቃላይ 13 ጊዜ ተገናኝተው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 4 ጊዜ ሲያሸንፍ አርባምንጭ ከተማ በ3 ጨዋታዎች ድል ቀንቶታል
በተቀሩት ስድስቱ ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ንግድ ባንክ 18 ግቦች፣ አርባምንጭ 15 ጎሎችን አስቆጥረዋል።