ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ባህር ዳር ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ባህር ዳር ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና

የጣና ሞገዶቹን ከ ቡናማዎቹ የሚያፋልመው ተጠባቂ ጨዋታ የሳምንቱ መገባደጃ መርሐግብር ነው።

በሰላሣ አራት ነጥቦች 4ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ባህርዳር ከተማዎች በመጨረሻው ሳምንት ካስመዘገቡት የአቻ ውጤት መልስ ወደ ድል በመመለስ ደረጃቸውን ለማሻሻል ወሳኝ መርሐ-ግብር ያከናውናሉ።

በግቦች ታጅበው ቅዱስ ጊዮርጊስን በማሸነፍ ሁለተኛውን ዙር የጀመሩት የጣና ሞገዶቹ  በኢትዮጵያ ቡና ከደረሰባቸው ሽንፈት በኋላ በተደረጉና ፈታኝ ቡድኖች በገጠሙባቸው አምስት የጨዋታ ሳምንታት ከሽንፈት ቢርቁም በመጨረሻው ሳምንት የጣሏቸው ሁለት ነጥቦች ከመሪው የነበራቸው ልዩነት አስፍቶታል። መሪው መድን ነጥብ መጣሉ እንዲሁም የነገው ጨዋታ ከቡድኑ በሁለት ነጥብ ልዩነት የተቀመጠው ኢትዮጵያ ቡና መሆኑ ተከትሎ የጨዋታው ትርጉም ከፍ ያደርገዋል።
በውድድር ዓመቱ የባህርዳር ከተማ ዋነኛው ድክመት በውጤት ረገድ ያለው የወጥነት ችግር ነው፤ በሀያ ሁለት ሳምንታት የሊጉ ቆይታቸው በአንድ አጋጣሚ ብቻ ተከታታይ ድል ያስመዘገበው ቡድኑ በዋንጫ ፉክክሩ ለመዝለቅ የተጠቀሰው ተከታታይ ድሎች የማስመዝገብ ድክመቱን መቅረፍ ግድ ይለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በመጨረሻው ጨዋታ የስሑል ሽረን የመከላከል አደረጃጀት ሰብሮ ዕድሎች በመፍጠር ረገድ ውስን ክፍተቶች የታየበት ቡድኑ በነገው ዕለት በስድስት ተከታታይ ሳምንታት መረቡን ያላስደፈረው ጠንካራው የቡና የመከላከል ጥምረት እንደመግጠሙ በማጥቃቱ ረገድ ተሻሽሎ መቅረብ ይኖርበታል።

በሰላሣ ስድስት ነጥቦች 3ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች በዋንጫ ፉክክሩ አንድ ደረጃ ከፍ ብሎ ለመፋለም ከነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማግኘት ግድ ይላቸዋል።

በሊጉ አናት ከሚገኘው መድን በዘጠኝ ነጥቦች ልዩነት የተቀመጠው ቡድኑ በነገው ዕለት ድል የሚቀናው ከሆነ የነጥብ ልዩነቱ  ወደ ስድስት የማጥበብ ዕድል በእጁ ይገኛል፤ ይህንን ተከትሎ ያላቸውን ልዩነት ለማጥበብ ሦስት ነጥብን እያለሙ ወደ ሜዳ ይገባሉ። ባለፉት ሰባት ጨዋታዎች ሽንፈት ያልቀመሱት ቡናማዎች በተለይም በመከላከሉ ረገድ ያላቸውን ጥንካሬ ቡድኑን ይበልጥ አጎልብቶታል። ባለፉት ስድስት ተከታታይ ጨዋታዎች መረባቸውን ባለማስደፈር መዝለቃቸውም የመከላከል ጥንካሬው ማሳያ ነው። ከመድን ቀጥለው በሊጉ ጥቂት ግቦች በማስተናገድ በ2ኛ ደረጃነት የተቀመጡት ቡናማዎቹ በተለይም በቅርብ ሳምንታት በመከላከሉ ረገድ የሚያስደንቅ ስራ መስራት ቢችሉም በማጥቃቱ በኩል ያላቸው ጥንካሬ ግን ደረት የሚያስነፋ አይደለም።  ባለፉት አስራ ሁለት ጨዋታዎች ውስጥ በአንድ አጋጣሚ ብቻ በጨዋታ ከአንድ ግብ በላይ ያስቆጠረው ቡድኑ በቀጣይ በሚደረጉ ወሳኝ መርሐ-ግብሮች ላለበት የዋንጫ ፉክክር የሚመጥን ስልነት መላበስ ግድ ይለዋል።

ከቀናት በፊት መሪው የጣላቸው ሁለት ነጥቦች የዚህን ጨዋታ ዋጋ ይበልጥ ከፍ የሚያደርግ ሲሆን በተጨማሪም በሁለቱም ቡድኖች መሀል ያለው የነጥብ ልዩነት ጨዋታው አጓጊ ያደርገዋል። ሁለቱም ቡድኖች ባላቸው የመከላከል ጥንካሬ አንፃር ግን ምናልባትም ጨዋታው በግቦች የታጀበ እንዳይሆን ሊያደርገው ይችላል።

የጣና ሞገዶቹ ከቅጣትም ሆነ ከጉዳት ነፃ የሆነ ስብስባቸውን ይዘው ሲቀርቡ በቡናማዎቹ በኩልም በተመሳሳይ ዲቫይን ዋቹኩዋ ቅጣቱን ጨርሶ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ መሆኑን ተከትሎ ሙሉ የቡድን አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለ11 ጊዜያት ተገናኝተው ባህር ዳር ከተማ 4 ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ 2 ጊዜ ድል ሲያደርጉ አምስቱ ጨዋታዎች አቻ የተጠናቀቁ ናቸው። በግንኙነታቸውም ባህር ዳር ከተማ 19 ኢትዮጵያ ቡናም በተመሳሳይ 19 ግቦችን አስቆጥረዋል።