ሪፖርት | ሀምራዊ ለባሾቹ እና አዞዎቹ ነጥብ ተጋርተዋል

ሪፖርት | ሀምራዊ ለባሾቹ እና አዞዎቹ ነጥብ ተጋርተዋል

በ24ኛ ሳምንት የመጨረሻ የጨዋታ ዕለት ቀዳሚው መርሃግብር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ከአርባምጭ ከተማ ጋር ያገናኘው ጨዋታ አንድ አቻ ተፈፅሟል።

ሀምራዊ ለባሾቹ ሲዳማ ቡናን 2-1 ሲያሸነፉ ከተጠቀሙበት ስብስብ ባደረጉት የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ፈቱዲን ጀማል ፣ ካሌብ አማንክዋሀ እና ሃይከን ደዋሙ አስወጥተው ተስፋዬ ታምራት፣ ዳዊት ዮሐንስ እና ሱሌይማን ሀሚድ ተክተው ሲገቡ በአንፃሩ አዞዎቹ ኢትዮ ኤሌክትሪክን 2-0 ካሸነፉበት ስብስብ ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ አህዋብ ብርያንን በታምራት እያሱ ብቻ ቀይረው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

በዋና ዳኛ መስፍን መሪነት የጀመረው ጨዋታው ዝግ ያለ አጀማመር ያስመለከተን ሲሆን በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ለመውሰድ ከሚደረጉ ፉክክሮች ውጪ እስከ 20ኛው ደቂቃዎች ድረስ የግብ ዕድሎችን አላስመለከተንም። ይሁን እንጂ በተደራጀ እንቅስቃሴ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ንግድ ባንኮች የተሻሉ ነበሩ። 23ኛው ደቂቃ ከሱሌይማን ሀሚድ የተሻገረለትን ኳስን ሳጥን ውስጥ በጥሩ ሁኔታ በደረቱ ያወረደው ዳዊት ዮሐንስ የመጨረሻው ውሳኔው ትክክል ባለመሆኑ ኳሷን ወደ ሰማይ የላካት ለሀምራዊ ለባሾቹ ለጎል የተቃረቡበት አጋጣሚ ነበር።

በሁለቱም በኩል ተመጣጣኝ የሆነ እንቅስቃሴ እያስመለከቱን በቀጠለው ጨዋታ 38ኛው ደቂቃ ላይ ንግድ ባንኮች ሳይመን እና ሱሌይማን በሜዳው ቀኝ መስመር እየተቀባበሉ ወደ ሳጥን የገባው ሱሌይማን ወደ ውስጥ የላከውን ሳይሞን ወደ ጎል የመታውን ግብ ጠባቂው ኢዲሪስ አምክኖበታል።

በጨዋታው እንቅስቃሴ ውስጥ ቢገኙም ሙከራዎችን ለማድረግ በኩል ብዙ ደቂቃዎች የጠበቁት አዞዎቹ በመጀመርያ ሙከራቸው 41ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አግኝተዋል። ቻርልስ ሪባኑ ከሜዳው የቀኝ የመሐል ክፍል በጥሩ ዕይታ በግራ መስመር ነፃ አቋቋም ላይ ለሚገኘው ታምራት እያሱ የላከለትን ኳሱን በተገቢው መንገድ ኳሱን ተቆጣጥሮ ከግብጠባቂው ፍሬው ጌታሁን አናት ላይ ኳሷን አሳልፎ መረብ ላይ አስቀምጦታል።

ከዕረፍት መልስ በቁጥር በዝተው ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በመድረስ ተጭነው መጫወታቸውን የቀጠሉት ንግድ ባንኮች ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ ወደ ጨዋታው የተመለሱበትን የአቻነት ጎል 60ኛው ደቂቃ ላይ አግኝተዋል። መነሻውን ከዘላለም የተነሳውን ኳስ ሱሌይማን ሳጥን ውስጥ ያሻገረለትን ሳይመን በግንባሩ ያቀበለው ዳዊት ዮሐንስ ኳሷን ደገፍ አድርጎ ወደ ጎልነት ቀይሯታል።

የማጥቃት ኃይላቸውን አጠናክረው የቀጠሉት ሀምራዊ ለባሾቹ 75ኛው ደቂቃ በቅብብሎች ሳጥን ውስጥ በመግባት ሱሌይማን ወደ ውስጥ የላከውን ዳዊት ዮሐንስ ያደረገው ሙከራ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።

አዞዎቹ በመከላከል ላይ አመዝነው በመልሶ ማጥቃት በረጅሙ በሚላኩ ኳሶች አደጋ ለመፍጠር በሚሞክሩም ስኬታማ ባልሆኑበት እንቅስቃሴ ውስጥ ተከላካይ ብሩክ ባይሳ ባሲሩ ኡመር ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ መውጣቱ አርባምንጮችን የበለጠ ጫና ውስጥ ከቷቸዋል። በቀሪ ደቂቃዎች በሁለቱም በኩል አህመድ ሁሴን በተጨማሪ ደቂቃ ከፈጠረው የጎል አጋጣሚ በቀር የተለየ ነገር ሳንመለከት ጨዋታው 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል።