ባህር ዳር ከተማዎች ኢትዮጵያ ቡናን 2ለ0 በማሸነፍ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከፍ ብለዋል።
12 ሰዓት ሲል በዋና ዳኛ ሄኖክ አበበ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ የጣና ሞገዶቹ ገና በ10ኛው ደቂቃ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። አምሳሉ ጥላሁን ከእጅ ውርወራ ያስጀመረውን ኳስ ሙጅብ ቃሲም በግንባር ገጭቶ ለቸርነት ሲያቃብለው የመስመር አጥቂው በሳጥኑ የግራ ክፍል ይዞት የገባውን ኳስ ወደ ውስጥ ሲያሻግረው ግብ ጠባቂው ዳንላድ ኢብራሂም ኳሱን ለማውጣት ሲሞክር ተቆርጦበት ኳሱ መረብ ላይ አርፏል።
ጎል ካስቆጠሩ በኋላም በተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ የቀጠሉት ባህር ዳሮች 12ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ሙጅብ ቃሲም ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ለሌላኛው የቡድን አጋሩ ፍሬው ሰለሞን ሰጥቶት ፍሬው ያደረገውን ሙከራም ግብ ጠባቂው ዳንላድ ኢብራሂም በፍጥነት ወደ ጎሉ በመመለስ በድንቅ ሁኔታ አግዶበታል።
ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ያደረጉት ቡናማዎቹ የመጀመሪያ ሙከራቸውን 16ኛ ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ ይታገሱ ታሪኩ ከረጅም ርቀት በጥሩ ሁኔታ አክርሮ የመታው ኳስ ከግቡ አግዳሚ ከፍ ብሎ ወጥቶበታል።
በጥሩ ፉክክር እየታጀበ በቀጠለው ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናዎች በጨዋታው የመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራቸውን 24ኛ ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ ዲቫይን ዋቹኩዋ ከአንተነህ ተፈራ በተቀበለው ኳስ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዶ መልሶበታል። አማካዩ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም ከቅጣት ምት በቀጥታ የመታው ኳስ በተመሳሳይ በግብ ጠባቂው ተመልሶበታል። በቀሪ ደቂቃዎችም ከመጠነኛ ፉክክር ውጪ የሚጠቀሱ የግብ ዕድሎች ሳይፈጠሩ ጨዋታው ወደ ዕረፍት አምርቷል።
ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ በሙከራ ረገድ ቀዳሚ የነበሩት የጣና ሞገዶቹ ነበሩ። 49ኛው ደቂቃ ላይ ቸርነት ጉግሳ ከራሱ የግብ ክልል በረጅሙ ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ሙጂብ ቃሲም ኳሱ ዓየር ላይ እንዳለ ግሩም ሙከራ ቢያደርግም በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ወጥቶበታል።
በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ለመውሰድ ከሚደረጉ ፍልሚያዎች ውጪ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል በመጠኑ እየተቀዛቀዘ በሄደው ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናዎች 67ኛው ደቂቃ ላይ ያለቀለት የግብ ዕድል አግኝተው ነበር። ኦካይ ጁል ከመሃል ሜዳ የሰነጠቀለትን ኳስ ያገኘው አንተነህ ተፈራ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዶ መልሶበታል።
ጨዋታው 70ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ የጣና ሞገዶቹ መሪነታቸውን ያጠናከሩበትን ጎል አስቆጥረዋል። ቸርነት ጉግሳ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ወንድወሰን በለጠ ከተከላካይ ጋር ተግሎ ያመቻቸለትን ተቀይሮ የገባው ፍጹም ዓለሙ ኳሱን መረቡ ላይ አሳርፎታል።
ኢትዮጵያ ቡናዎች ወደ ጨዋታው ሊመልሳቸው የሚችል ዕድል 75ኛ ደቂቃ ላይ አግኝተው ኮንኮኒ ሀፊዝ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ያደረገው ሙከራ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ሲወጣበት 87ኛ ደቂቃ ላይ የባህር ዳር ከተማው አቤል ማሙሽ ከረጅም በተጣለለት ኳስ ያደረገው ሙከራ በግቡ የግራ ቋሚ ለጥቂት ወጥቶበታል። ይህም የተሻለው የመጨረሻ የግብ ሙከራ ሆኖ ጨዋታው በባህር ዳር ከተማ 2ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።