በሰንጠረዡ ግርጌ ተከታትለው የተቀመጡት ቡድኖችን የሚያፋልመው ጨዋታ የ25ኛው ሳምንት መክፈቻ መርሐ-ግብር ነው።
ከቀናት በፊት ከአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ጋር የተለያየው ወልዋሎ በዓመቱ ከተደረገው ሦስተኛው የአሰልጣኝ ለውጥ በኋላ የመጀመርያ ጨዋታውን ያደርጋል።
በአስር ነጥቦች በሊጉ ግርጌ ከሚገኘው
ወልዋሎ ዓመቱን ከአሠልጣኝ አሸናፊ በቀለ ጋር ቢጀምርም በሰባተኛው ሳምንት ከአሰልጣኙ ጋር ተለያይቶ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያምን መቅጠሩ ይታወሳል፤ አሁን ደግሞ በውድድር ዓመቱ ለሦስተኛ ጊዜ የሹም ሽር አድርጎ እስከ ውድድር ዓመቱ ፍፃሜ ድረስ በአሰልጣኝ አታኽልቲ በርኸ እንደሚመራ ታውቋል። ቢጫዎቹ በነገው ዕለት የሚኖራቸው አቀራረብ ለመገመት አዳጋች ቢሆንም ለቡድኑ እዚህ ደረጃ ላይ መገኘት ምክንያት ለሆኑት የመከላከል እና የማጥቃት ድክመቶች መፍትሔ ማበጀት የአዲሱ አሰልጣኝ ቀዳሚ ስራዎች መሆን ይኖርባቸዋል። በተለይም በመከላከሉ ረገድ የሚስተዋሉት ጉልህ ግለ-ሰባዊ ስህተቶች እንዲሁም ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች በሁለት አጋጣሚዎች ቡድኑን ዋጋ ያስከፈሉ አላስፈላጊ የቀይ ካርዶች መቀነስ አለባቸው።
በአስራ ስድስት ነጥቦች 17ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ስሑል ሽረዎች ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል ለመመለስ ወልዋሎን ይገጥማሉ።
የነገው ጨዋታ ለስሑል ሽረ የደረጃ ማሻሻያ ምክንያት ባይሆንም ከበላዩ ካለው ሀዋሳ ከተማ ያለው የአምስት ነጥብ ልዩነት የማጥበብ ዕድል ሊሰጠው ይችላል ። ከነገው ተጋጣሚያቸው በስምንት ነጥቦች ልቀው የተቀመጡት እና ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ተከታታይ ድሎች ማስመዝገብ ግድ የሚላቸው ሽረዎች ወደ ሚፈልጉት የድል ጎዳና ለመመለስ ጉልህ የግብ ማስቆጠር ችግራቸው መፍታት ይኖርባቸዋል። የነገው ተጋጣሚው ወልዋሎ ድል ካደረገበት የ19ኛው ሳምንት መርሐ-ግብር በኋላ በተከናወኑ አምስት ጨዋታዎች ኳስና መረብ ማገናኘት ያልቻለው ቡድኑ የውድድር ዓመቱ ጉዞው በጥቅሉ ሲታይ ከፍተኛ የሆነ የግብ ማስቆጠር ድክመት የታየበት ነበር። የአሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት ቡድን ከባህርዳር ከተማ ጋር ነጥብ በተጋራበት እንዲሁም በሲዳማ ቡና ሽንፈት ባስተናገደበት ጨዋታ ውስን መሻሻል ማሳየት ቢችልም ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ለግብ ማስቆጠር ችግሩ መፍትሔ ማበጀት ይጠበቅበታል።
በወልዋሎ በኩል ሙሳ ራማታ እና ፉዐድ አዚዝ በቅጣትም ምክንያት አይሰለፉም አምበሉ በረከት አማረም ከጉዳት ተመልሶ ልምምድ ቢጀምርም በነገው ጨዋታ የመሰለፉ ነገር አልተረጋገጠም።
ስሑል ሽረዎች በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም።
ሁለቱ ቡድኖች በፕሪምየር ሊጉ 3 ጊዜ ተገናኝተው ስሑል ሽረ 2 ጊዜ ድል ሲቀናው ወልዋሎ 1 አሸንፏል። በአጠቃላይ 5 ጎሎች ሲቆጠሩ ስሑል ሽረ 3 ወልዋሎ ደግሞ 2 ግብ አስቆጥረዋል። (የተሰረዘው 2012 ጨዋታ አልተካተተም)።