ሀድያ ሆሳዕን እና መቐለ 70 እንደርታ በዕለተ ሆሳዕና የሚያደርጉት ጨዋታ 12:00 ይጀመራል።
ሰላሣ አራት ነጥቦች ሰብስቦ 6ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው እና በላይኛው የሰንጠረዡ ክፍል ካለው ፉክክር ላለመራቅ ድል ማድረግ አስፈላጊው የሆነው ሀድያ ሆሳዕና ከድል ጋር ከተራራቀ አምስት የጨዋታ ሳምንታት ተቆጥረዋል። ካለፉት አስር ተከታታይ ጨዋታዎች በሁለቱ ብቻ ሙሉ ነጥብ ያስመዘገበው ቡድኑ ደረጃውን ለማሻሻል ጉዞውን በውጤት ማጀብ ከምንም በላይ አስፈላጊው ነው።
ነብሮቹ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው አስራ አምስት ነጥቦች አራቱን ብቻ አሳክተዋል፤ ቡድኑ በግብ ማስቆጠር በኩል ያለው ድክመትም በውጤት ረገድ ለገጠማቸው መንሸራተት እንደምክንያት ይነሳል። በመጀመሪያው ዙር በተሻለ ጥንካሬ ላይ የነበረው የፊት መስመሩ አሁን በሚፈለገው መጠን ግቦችን እያስቆጠረ አለመሆኑ ከነገው ጨዋታ በፊት መሻሻል የሚገባው የቡድኑ ደካማ ጎን ሆኗል። ባለፉት አምስት ጨዋታዎች በሁለት አጋጣሚዎች ብቻ ኳስና መረብ ያገናኙት ነብሮቹ ከሳምንታት ቆይታ በኋላ ከድል ጋር ለመታረቅ ዋነኛ ድክመታቸው የሆነው የግብ ማስቆጠር ችግር መፍታት አለባቸው።
በሀያ አምስት ነጥቦች 14ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት መቐለ 70 እንደርታዎች ካንዣበበባቸው አደጋ ለመራቅ ከነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማግኘት አስፈላጊያቸው ነው።
በሁለተኛው ዙር ካደረጓቸው አምስት ጨዋታዎች አራት ሽንፈት እና አንድ ድል ያስመዘገቡት ምዓም አናብስት ካሉበት የስጋት ቀጠና ለመራቅ እና በአራት ነጥቦች ልዩነት ተከታትለው ከተቀመጡት ክለቦች ለማምለጥ ነገ አሸንፈው መውጣት የግድ ይላቸዋል። በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ተከታታይ ሽንፈት የገጠመው ቡድኑ በተለይም በመጨረሻው ጨዋታ በማጥቃቱ ረገድ ውስን መሻሻሎች ማሳየት ቢችልም በቂ የግብ ዕድሎች በመፍጠር ረገድ ያለበት ድክመት ግን አሁንም መቅረፍ አልቻለም፤ የቡድኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ያሬድ ብርሀኑ ከጉዳት መልስ ለጨዋታ ዝግጁ መሆኑ ለምዓም አናብስቱ መልካም ዜና ቢሆንም በቀጣይ በሦስተኛው የሜዳ ክፍል የሚታይባቸው የቁጥር ማነስ ማመጣጠን ግን ወሳኝነቱ ትልቅ ነው።
ከዚህ በተጨማሪም በመከላከሉ በአንዳንድ የጨዋታ ቅፅበቶች ላይ የሚታይባቸው የትኩረት መውረድ እንደ ነገ ባለ ውጤቱን አጥብቆ በሚሻ ተጋጣሚ እንዲቀጡ ምክንያት ሊሆን ይችላል። በመሆኑም አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ ቡድናቸው በተለይም በሽግግሮች ወቅት ባልተዛነፈ ትኩረት ውስጥ ጨዋታውን እንዲከውን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
በነብሮቹ በኩል ብሩክ ማርቆስ ከቅጣት ከመመለሱ ውጭ አስቀድመው ጉዳት ላይ የነበሩት በረከት ወንድሙ፣ ጫላ ተሺታ ፣ መለሰ ሚሻሞ እና ሄኖክ ሀርፊጮ አሁንም ለነገው ለጨዋታ አየደደርሱም። ከዚህ ውጭ ስብስቡ እንዳለ ሆኖ ለነገው ጨዋታ የሚፋለም ይሆናል። በመቐለ 70 እንደርታ በኩል ያሬድ ብርሃኑ እና ተመስገን በጅሮንድ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ሲሆኑ ሔኖክ አንጃው ግን አሁንም ከጉዳቱ አላገገመም።
ቡድኖቹ በሊጉ ሦስት ጊዜ ተገናኝተዋል፤ ምዓም አናብስቱ በ 2 ድል ሲቀናቸው ነብሮቹ 1 ጨዋታ አሸንፈዋል። መቐለ 70 እንደርታ 3 ግቦች ስያስቆጥር ሀድያ ሆሳዕና 2 አስቆጥሯል።