ሪፖርት | መቐለ 70 እንደርታ ሀዲያ ሆሳዕናን ማሸነፍ ችሏል

ሪፖርት | መቐለ 70 እንደርታ ሀዲያ ሆሳዕናን ማሸነፍ ችሏል

ምዓም አናብስት ነብሮቹን 2-0 በማሸነፍ  ከሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ድል ማድረግ ችለዋል።

በኢዮብ ሰንደቁ

25ኛ ሳምንቱን ባስቆጠረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድሩን በሐዋሳ ከተማ ማድረጉን የቀጠለው ውድድር ምሽት 12፡00 ሲል ሀዲያ ሆሳዕናን ከ መቐለ 70 እንደርታ አገናኝቷል። ሀዲያ ሆሳዕናዎች ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ግብ ጠባቂያቸውን ሚካኤል ሳማኪን በያሬድ በቀለ፣ ከማል ሀጂን በብሩክ ማርቆስ እና ኢዮብ ዓለማየሁን በብሩክ በየነ በመቀየር ሲገቡ በተመሳሳይ መቐለ 70 እንደርታዎች በመቻል ሽንፈት ካስተናገዱበት አሰላለፍ የአብሥራ ተስፋዬ እና ቦና አሊን በማሳረፍ በምትካቸው ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ እና ንኮዋ ሐፕሞን አስገብተው ጨዋታቸውን ጀምረዋል።

ሁለቱን ቡድኖች ባገናኘው የምሽቱ ጨዋታ በእንቅስቃሴ እና በማጥቃቱ ረገድ መቐለዎች የተሻሉ ነበሩ። በረጅም ከሚጣሉ ኳሶች ግቦችን ለማግኘት ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት መቐለዎች ጥሩ ጥረትን ቢያደርጉም ግን በግቡ ሶስተኛ ክፍል ላይ በሚያሳዩት ደካማ የሆነ አጨራረስ ምክንያት ጎል ማስቆጠር ተስኗቸዋል። በተቃራኒው በተጋጣሚ ብልጫ የተወሰደባቸው ሀድያዎች በመከላከል የሚገኙትን ኳስ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ሙከራ ሲያደርጉ ነበር።

እንዲህ እያለ የቀጠለው ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች ይህ ነው የሚባል ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳያስመለክቱን ረዘም ያለ ደቂቃ ቢያስጠብቁንም የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ የዳኛው ፊሽካ በሚጠበቅበት ሰዓት 45+2′ ላይ ሄኖክ አዱኛ ከማዕዘን ያሻማውን ኳስ ቤንጃሚን ኮቴ በግንባሩ በመግጨት ወደ ግብነት ቀይሮ ምዓም አናብስቶችን መሪ ማድረግ ችሏል። ይህንንም ተከትሎ 1-0 በሆነ ውጤት የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ በጨዋታ ረገድ ተሽለው የነበሩት መቐለ 70 እንደርታዎች ሲሆኑ ሀድያ ሆሳዕናዎችም ከስህተት የሚገኙ ኳሶችን በመልሶ ማጥቃት ተጠቅመው ግብ ለማግኘት ሙከራ ማድረጋቸውን የቀጠሉ ሲሆን በዚህም ተመስገን ብርሃኑ በቀኝ በኩል ወደ ሳጥን ይዞ ገብቶ የሞከረው እና ግብጠባቂው ሶፎንያስ የመለሰበት ኳስ ተጠቃሽ ነው።

በአመዛኙ መቐለ 70 እንደርታዎች ኳስን መስርተው በሽግግር መጫወት ሲችሉ በተመሳሳይ ሀድያ ሆሳዕናዎች ወደ መስመር በሚጣሉ ኳሶች መነሻነት የአቻነት ግብ ፍለጋቸውን ማድረግ የቻሉ ቢሆንም እንደ መጀመሪያው አጋማሽ በሁለቱም በኩል በሙከራ ረገድ ይህ ነው የሚባል ሙከራ ሳያሳዩን ረዘም ያለ ደቂቃዎችን አስቆጥረዋል።

79ኛው ደቂቃ ላይ መነሻውን ከቀኝ መስመር ያደረገው ኳስ በጥሩ አንድ ሁለት ቅብብል ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በመግባት አሸናፊ ሐፍቱ ያቀበለውን ኳስ ብሩክ ሙሉጌታ ጥሩ የሆነ ግብ አስቆጥሮ መሪነቱን በሁለት ጎል ልዩነት ከፍ ማድረግ ችሏል። ይህንንም ተከትሎ ጨዋታው በመቐለ 70 እንደርታ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።