ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

በአንድ ነጥብ ልዩነት የተቀመጡትን የመዲናይቱ ክለቦች የሚያገናኘው ተጠባቂ ጨዋታ ረፋድ ላይ ይከናወናል።

በሰላሣ አንድ ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከናፈቃቸው ድል ጋር ለመታረቅ ከቅርብ ተፎካካሪያቸው ጋር ይፋለማሉ።

ፈረሰኞቹ ድል ካደረገሩ ሰባት የጨዋታ ሳምንታት አስቆጥረዋል። የመጀመሪያው ዙር ወጥ አቋሙን ማስቀጠል ያልቻለው ክለቡ በሁለተኛው ዙር ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች ድል ማድረግ አልቻለም፤ ማግኘት ከሚገባው 15 ነጥብ ውስጥም 2 ብቻ ነው ማሳካት የቻለው። በመሆኑም ከበታቹ ያሉት ክለቦች ሳይጠጉት በፊት ነጥቡን ከፍ አድርጎ መደላደል ይጠበቅበታል። ከነገው ጨዋታ ውጤት ማግኘት መቻል ለፈረሰኞቹ  ከውጤትም በላይ ፋይዳው ብዙ ነው፤ በተከታታይ ጨዋታዎች ድል ማድረግ ያልቻለው እና በመጨረሻው መርሐግብር በፋሲል ከነማ ከገጠመው ሽንፈት ለማገገም ወደ ሜዳ የሚገባው ቡድኑ በነገው ዕለት ድል ማድረግ በደረጃ ሰንጠረዡ ከሚያገኘው መሻሻል በተጨማሪ በቀሩት ጨዋታዎች በሥነ ልቦናው ጠንክሮ እንዲቀርብ የሚያደርገው ጉዳይ ነው።

ይህ እንዲሳካ ግን ዘርፈ ብዙ መሻሻሎች ማድረግ ከቡድኑ ይጠበቃል፤ ፈረሰኞቹ ለሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ኳስ እና መረብ ማገናኘት ከተሳናቸው በኋላ በመጨረሻው መርሐግብር ግብ ማስቆጠር ቢችሉም የማጥቃት ክፍላቸው አሁንም መሻሻል ይኖርበታል፤ ግቦች የሚገኙባቸውን አማራጮች ማስፋት እንዲሁም የሚገኙ ጨዋታ ቀያሪ ዕድሎች በመጠቀም ረገድ ያለው ክፍተትም ከነገው ጨዋታ በፊት መቀረፍ የሚገባው ጉዳይ ነው።

በሁለተኛው ዙር መነቃቃትን ካሳዩ ቡድኖች መካከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሁለተኛው ዙር ከአንድ ሽንፈት ውጪ በሰበሰባቸው ነጥቦች ወደ ሰንጠረዡ ወገብ ለመድረስ እየጣረ ይገኛል።

በሰላሣ ሁለት ነጥቦች 9ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው እና ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ከ15 ነጥቦች አስሩን ማሳካት የቻለው ቡድኑ ከሰንጠረዡ አጋማሽ ከፍ ብሎ ለመፎካከር ከነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ መሰብሰብ አስፈላጊው ነው። ባለበት ቀጠና ካለው የነጥብ መቀራረብ አንፃርም በነገውን ጨዋታ ድል ማድረግ ደረጃውን የማሻሻል ዕድል ይኖረዋል። ባለፉት አስር ጨዋታዎች በሁለት አጋጣሚዎች ብቻ
ሽንፈት የቀመሱት ሀምራዊ ለባሾቹ  ከሽንፈት መራቃቸው፤ ትርጉም ያላቸው የማጥቃት ሂደቶችን በማሳየት ተጋጣሚን ጫና ውስጥ የሚከቱባቸው አጋጣሚዎችም እንዲሁ ቀስ በቀስ እድገት ማሳየት መጀመራቸው እና ጨዋታን የመቆጣጠር የወትሮ ጥንካሬያቸው ማስቀጠላቸው ከተጠባቂው ጨዋታ በፊት የተሻለ ግምት እንዲሰጣቸው የሚያስገድድ ነው። ቡድኑ በማጥቃቱ ረገድ ከባድ ፈተና ይገጥመዋል ተብሎ ባይገመትም ሁለቱ ወሳኝ ተከላካዮች ካሌብ አማንክዋህ እና ፈቱዲን ጀማል ከነገው ጨዋታ ውጭ የመሆናቸው ጉዳይ ግን ለሀምራዊ ለባሾቹ ጥሩ ዜና አይደለም።

በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ተገኑ ተሾመ ፣ ሻይዱ ሙስጠፋ ፣ ፍሪምፖንግ ክዋሜ እና አብዱልሃፊዝ ቶፊቅ በጉዳት ምክንያት ወደ ሀዋሳ ካልተጓዘው የቡድን አባላት ሲሆኑ ባለፈው ሳምንት የነበሩት አስራ ስምንት ተጫዋቾች አሁንም ለነገው ጨዋታ ዝግጁ መሆናቸው ታውቋል። በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል አምበሉ ፈቱዲን ጀማልን ጨምሮ ሌላው ተከላካይ ካሌብ አማንክዋሀ በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆኑ ለሦስት ሳምንታት በጉዳት ምክንያት ያልነበረው የመስመር አጥቂው አዲስ ግደይ በትናንትናው ዕለት ልምምድ የጀመረ ቢሆንም ለነገው ጨዋታ እንደማይደርስ ተሰምቷል። ሌሎቹ የቡድኑ አባላት ግን ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።

ተጋጣሚዎቹ በሊጉ በነበራቸው 38 ያህል ግንኙነቶች ቅዱስ ጊዮርጊስ ከፍተኛ የበላይነት ያለው ሲሆን 25 አሸንፎ ፣ በ10 ጨዋታ አቻ ተለያይተው ንግድ ባንክ 3 ጨዋታ አሸንፏል። ፈረሰኞቹ 71 ጎሎች ሲያስቆጥሩ ሀምራዊዎቹ 22 ጎሎች አስቆጥረዋል። በግንኙነታቸው ንግድ ባንክ ለመጨረሻ ጊዜ ያሸነፈው በ1998 ዓ/ም ነበር።