የመጨረሻው ሳምንት ድላቸውን ለማስቀጠል የሚፋለሙት ሲዳማ ቡና እና ባህር ዳር ከተማ የሚያገናኘው ጨዋታ 9:00 ይጀመራል።
ስሑል ሽረን አንድ ለባዶ በማሸነፍ ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ ከድል ጋር የታረቁት ሲዳማ ቡናዎች ነጥባቸው ሃያ ዘጠኝ በማድረስ ከስጋት ቀጠናው ፈቀቅ ብለዋል። በሁለተኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው ባህር ዳር ከተማ ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ ድል ማድረግ ከቻሉም ከአስራ ስድስት የጨዋታ ሳምንታት በኋላ ተከታታይ ድል በማስመዝገብ ከአደጋው ቀጠና ይበልጥ የመራቅ ዕድል ይኖራቸዋል። ሲዳማ ቡና ቡናዎች ስሑል ሽረን ባሸነፉበት እንዲሁም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሽንፈት ባስተናገዱበት ጨዋታ ጭምርም የተሻለ ጫና በመፍጠር በማጥቃቱ ረገድ የሚታይ መሻሻል ማሳየታቸው በአወንታዊ ጎኑ የሚነሳላቸው ነጥብ ቢሆንም አሁንም በሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ የሚሰሯቸው የቅብብል እና የውሳኔ አሰጣጥ ስህተቶች ማስተካከል ይጠበቅባቸዋል።
በነገው ዕለት ጠንካራ የኋላ ክፍል ያለው ቡድን
እንደመግጠማቸው በማጥቃቱ ረገድ ከሚጠበቀው መሻሻል በተጨማሪ በመከላከሉ ረገድም ተመሳሳይ ነገር ይጠበቃል። የቡድኑ የኋላ ክፍል ከጀርባው ክፍተት በሚተውባቸው ቅፅበቶች በተለይም በቸርነት ጉግሳ በሚመራው የተጋጣሚ ዋነኛ የማጥቂያ መስመር የበዛ ጫና ሊያስተናግድ ይችላል፤ ቡድኑ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሽንፈት ባስተናገደት ጨዋታ በተጠቀሰው ስህተት በመጨረሻ ደቂቃ ግብ እንደማስተናገዱ በቀጣይ መሰል ስህተቶችን ማረም ይኖርበታል።
በሰላሣ ሰባት ነጥቦች 2ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት
ባህርዳር ከተማዎች በዋንጫ ፉክክሩ እያደረጉት ያሉት ፍልሚያ ለማስቀጠል በነገው ዕለት ድል ማድረግ እጅግ አስፈላጊያቸው ነው።
ከመሪው ጋር በስምንት ነጥብ ልዩነት የሚገኙት የጣና ሞገዶቹ በዋንጫ ፉክክር ለመዝለቅ በቀዳሚነት የወጥነት ችግራቸውን መቅረፍ ይኖርባቸዋል። ቡድኑ ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች ከሽንፈት መራቁ እንዲሁም ፈታኝ በነበሩት የቅርብ ሳምንታት መርሐግብሮች ያሳየው የሚበረታታ እንቅስቃሴ በዋንጫ ፉክክሩ ረዥም ርቀት መሄድ እንደሚችል ጠቋሚ ቢሆኑም በውድድር ዓመቱ እስካሁን ድረስ ተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ድል ያለማድረጉ ጉዳይ ግን ከወዲሁ መስተካከል የሚገባው ነው። ቡድኑ በተከታታይ ስድስት ጨዋታዎች ግብ ሳያስተናግድ የዘለቀው ጠንካራው ኢትዮጵያ ቡና ላይ ሁለት ግቦች አስቆጥሮ ድል ባደረገበት ጨዋታ የነበሩት አወንታዊ ጎኖች በነገው ወሳኝ ፍልሚያ ማስቀጠል ጨዋታውን የማሸነፍ ዕድሉ የሚያሰፋለት ሲሆን ተጋጣሚው ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ካሳየው መሻሻል አንፃር ግን የሚጠብቀው ፈተና ቀላል እንደማይሆን መገመት ይቻላል።
በሲዳማ ቡና በኩል አንተነህ ተስፋዬ ወደ ልምምድ መመለሱ ለቡድኑ ጥሩ ዜና ሲሆን የተቀሩት የቡድኑ አባላትም ለነገው ጨዋታ ተሟልተው ይቀርባሉ። የጣና ሞገዶቹም ከቅጣትም ሆነ ከጉዳት ነፃ የሆነ ስብስባቸውን ይዘው ይቀርባሉ።
ተጋጣሚዎቹ እስካሁን በ11 የሊግ ጨዋታዎች ሲገናኙ ሲዳማ ቡና 5 ባህርዳር ከተማ ደግሞ 4 ጨዋታዎች ሲያሸንፉ 2 ጊዜ ነጥብ ተጋርተዋል። በጨዋታዎቹ ባህር ዳር 14 ሲዳማ ቡና ደግሞ 17 ግቦች አስቆጥረዋል።