ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ሀዋሳ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ሀዋሳ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ

በደረጃ ሰንጠረዡ በሁለት የተለያዩ ፅንፎች ባለ ፉክክር ወሳኝ ድል ለማስመዝገብ የሚፋለሙት ሀይቆቹ እና የጦና ንቦቹ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው

በሀያ አንድ ነጥቦች 15ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሀዋሳ ከተማዎች ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት በሚያደርጉት ጉዞ ወሳኝ የሆነውን ጨዋታ ያከናውናሉ።

በመጀመርያው ዙር የመጀመርያ ሦስት ጨዋታዎች ጥሩ እንቅስቃሴ አድርገው አምስት ነጥቦች መሰብሰብ ችለው የነበሩት ሀዋሳ ከተማዎች በ23ኛው ሳምንት በመሪው መድን ከገጠማቸው ሽንፈት አገግመው በመጨረሻው ጨዋታ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ነጥብ መጋራት ቢችሉም ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት የሚያደርጉት ጉዞ ለማሳለጥ  ድል ማድረግ አስፈላጊያቸው ነው።

ሀይቆቹ ከአሰልጣኝ ሙልጌታ ምሕረት ቅጥር በኋላ ጥሩ መሻሻል ማሳየታቸው አይካድም፤  ቡድኑ ከውጤቱ ባለፈ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴው ጥሩ እድገት ማሳየቱ እንዲሁም ባለፉት አምስት ጨዋታዎች በአንድ አጋጣሚ ብቻ ሽንፈት መቅመሱም እንደ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል።
ሆኖም ጨዋታዎች በአቻ ውጤት የማጠናቀቅ አባዜው አሁንም ከወራጅ ቀጠናው ፈቀቅ እንዳይል አድርጎታል። ቡድኑ በርካታ የአቻ ውጤት በማስመዝገብ ቀዳሚ ከሆነው ድሬዳዋ ከተማ በመቀጠል በብዙ ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቶ የወጣ ክለብ መሆኑ እንዲሁም በሁለተኛ ዙር ከተከናወኑ አምስት ጨዋታዎች ውስጥ ሦስቱ በአቻ ውጤት ማጠናቀቁ ከአቻ ውጤት መላቀቅ እንዳልቻለ ማሳያዎች ናቸው።

አሰልጣኝ ሙልጌታ ምሕረት ያመጣው ተስፋ ሰጪ ለውጥ በውጤት ለማጀብ የቡድኑ የአሸናፊነት መንፈስ ከፍ ከማድረግ በተጨማሪ ለግብ ማስቆጠር ድክመቱም መፍትሔ ማበጀትም አካሄዱን ለማስተካከል ይረዳዋል።

በሰላሣ ሰባት ነጥቦች በ2ኛ ደረጃ የተቀመጡት ወላይታ ድቻዎች ከመሪዎቹ ጎራ ላለመራቅ ዳግም ወደ ድል ለመመለስ እያለሙ ወደ ሜዳ ይገባሉ።

የብዙዎች ግምት በማፋለስ ሳይጠበቁ በዋንጫ ፉክክሩ የዘለቁት የጦና ንቦቹ ከአራት ተከታታይ ድሎች በኋላ በመጨረሻው ጨዋታ ነጥብ ተጋርተው ለመውጣት ቢገደዱም የባለፉት መርሐ-ግብሮች ብቃታቸው ብዙ የሚያስወድሳቸው ነበር። በሁለተኛው ዙር በተካሄዱ አምስት ጨዋታዎች ማሳካት ከሚገባቸው አስራ አምስት ነጥቦች ሁለቱን ብቻ ጥለው አስራ ሦስት ነጥብ ያገኙት የጦና ንቦቹ ከሚታይባቸው ውስን የግብ ማስቆጠር ድክመት ውጭ በብዙ መመዘኛዎች የላቀ ወቅታዊ ብቃት ላይ ይገኛሉ። ቡድኑ ከዋነኞቹ ድክመቶቹ አንዱ የነበረው የመከላከል ችግሩ ፈቶ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች መረቡን ማስከበሩ እንዲሁም ተጫዋቾቹ ውጤት ለማጠበቅ የሚያደርጉት ቡድኗዊ እንቅስቃሴ በዋንጫ ፉክክር እንዲገኙ ምክንያት ሆኗል፤ ሆኖም በዋንጫ ፉክክሩ እስከመጨረሻው ድረስ ለመፋለም የሚያስችል አስተማማኝ የፊት መስመር ጥንካሬ መንገንባት ከጦና ንቦቹ የሚጠበቅ ቀጣይ ተግባር ነው።

ካላቸው የስብስብ ጥራት እና ጥልቀት አንፃር ጥሩ ቡድን በመገንባት ወላይታ ድቻን በላይኛው የሰንጠረዡ ክፍል እንዲፎካከር ያስቻሉት የአሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ በቀጣይ ባለፉት አስር መርሐ-ግብሮች በጨዋታ ከአንድ ግብ በላይ ማስቆጠር ያልቻለው የማጥቃት አጨዋወታቸው ላይ ውስን ለውጦች ማድረግ ይኖርባቸዋል።

በሀዋሳ ከተማ በኩል ከእስራኤል እሸቱ  ውጪ ሁሉም የቡድን አባላት ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው። ወላይታ ድቻዎችም ከቅጣትም ይሁን ከጉዳት ነፃ የሆነው ስብስባቸው ይዘው ለጨዋታው ይቀርባሉ።

ሁለቱም ቡድኖች በሊጉ እስከ አሁን ለ21 ጊዜያት ያህል የተገናኙ ሲሆን በተመሳሳይ ቁጥር ሰባት ሰባት ጊዜ ተሸናንፈዋል። በሰባት አጋጣሚዎች ደግሞ አቻ ሲለያዩ ወላይታ ድቻ 22 ፤ ሀዋሳ ከተማ ደግሞ 25 ግቦችን በግንኙነታቸው አስቆጥረዋል።