ሪፖርት | የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ19 ዓመታት በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስን ረቷል

ሪፖርት | የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ19 ዓመታት በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስን ረቷል

ከ1998 የውድድር ዘመን በኋላ ሀምራዊ ለባሾቹ በሳይመን ፒተር ብቸኛ ግብ ፈረሰኞቹን በመርታት እጅግ አስፈላጊ ሦስት ነጥብ አሳክተዋል።


ቅዱስ ጊዮርጊስ ባሳለፍነው ጨዋታ ሳምንት በፋሲል ከነማ 2ለ1 ሽንፈት ሲያስተናግዱ ይዘው ከገቡት ቋሚ አሰላለፋቸው ሦስት ለውጦችን ሲያደርጉ በዚህም አሸናፊ ጌታቸው ፣ ጳውሎስ ከንቲባ እና ቢኒያም ፍቅሩን አሳርፈው በምትካቸው አማኑኤል ተርፋ ፣ አብርሃም ጌታቸው እና አማኑኤል ኤርቦን ይዘው ሲገቡ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በበኩላቸው ባለፈው ጨዋታ ሳምንት ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርተው ከወጡበት ቋሚያቸው ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ቀርበዋል።

ጥንቃቄ በተሞላ መንገድ ጅማሮውን ያደረገው የረፋዱ ጨዋታ በ3ኛው ደቂቃ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ኳስ ወደ ሳጥን በዳዊት ዩሐንስ አማካኝነት ይዘው በሚገቡበት ወቅት የፈረሰኞቹ ተከላካዮች በሰሩት ጥፋት በሳጥኑ ቅርብ ርቀት ላይ ቅጣት ምት አግኝተው ሳይመን ፒተር ጠንከር ያለ ኳስ ወደ ግብ ቢመታም የግብ ዘቡ ተመስገን ዩሐንስ ከያዘበት ሙከራ ውጪ ሌላ ተጨማሪ ሙከራ ሳያስመለክት የመጀመሪያዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች ተቆጥረውበታል።

በተደጋጋሚ የቆመ ኳስ እያገኙ እንዲሁም ወደፊት በመሄድ ረገድ ብልጫን መውሰድ የቻሉት ንግድ ባንኮች የጥረታቸው ውጤት የሆነችዋን ግብ 21ኛው ደቂቃ ላይ አግኝተዋል። ከቆመ ኳስ የተሻማችን ኳስ ተመስገን ጨርፎ ሲያወጣት የግብ ጠባቂውን መውጣት የተመለከተው ሳይመን ፒተር ኳሱን ከፍ አድርጎ በመጣል መረብ ላይ አሳርፎ መሪ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።

ከግቡ መቆጠር በኋላም ቡድኖቹ በመልሶ ማጥቃት በፈጣን ሽግግር ወደ ሶስተኛው ሜዳ ክፍል በመድረስ የግብ እድል ለመፍጠር ቢጥሩም ይሄ ነው የሚባል ጠንካራ የግብ ማግባት ሙከራ ሳያደርጉ ቆይተው በ28ኛው ደቂቃ ላይ አደገኛ ሙከራ ንግድ ባንኮች በሱሌማን ሀሚድ አማካኝነት አድርገዋል። በተጠቀሰው ደቂቃ በቀይ መስመር በኩል ሆኖ የመታው ኳስ ለትንሽ ከግቡ ቋሚ ብረት በኩል አልፎ ኢላማውን ሳይጠብቅ የቀረው ሙከራ ይጠቀሳል።

የአጋማሹ መደበኛው ደቂቃ ተጠናቆ ጭማሪ በታየው ላይ ዳዊት ዩሐንስ ተጨራርፎ ያገኘውን ኳስ እየገፋ በቁጥር የፈረሰኞቹን ተከላካዮች በልጠው ቢገቡም እራሱ ዳዊት ዩሐንስ ሳጥን ውስጥ ሆኖ መሬት ለመሬት ወደ ግብ ቢመታም ከግቡ ቋሚ ብረት ለትንሽ ርቆ ያለፈበት አጋጣሚ መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ አድርገው ወደ መልበሻ ክፍል እንዲገቡ ለማድረግ ቀርቦ የነበረ ቢሆንም ሳይጠቀሙበት ቀርተው አጋማሹ ተገባዷል።

ጨዋታው በሁለተኛ አጋማሽ ሲቀጥል ሁለቱም ቡድኖች የተጫዋች ቅያሪ አድርገው ወደ ሜዳ ተመልሰዋል። ጨዋታው ገና እንደጀመረ ተጨማሪ ግብ ማሰሳቸውን የቀጠሉት ባንኮች አከታተለው የግብ ማግባት ሙከራዎችን አደርገዋል፤ከእነዛም መካከል 47ኛው ደቂቃ ላይ ሳይመን ፒተር ላይ በተሰራ ጥፋት የቆመ ኳስ ሱሌማን ሀሚድ ቀጥታ ወደ ግብ መጥቶ ከግቡ አግዳሚ ብረት ለጥቂት ከፍ ብሎ ያለፈበት ፣ እንዲሁም 57ኛው ደቂቃ እራሱ ሱሌማን ሀሚድ በቀኝ መስመር በኩል ሆኖ ወደ ግብ ያሻገረውን ኳስ ኪቲካ ጅማ ሳይጠቀም የቀረበት አጋጣሚዎች ይጠቀሳሉ።

ፈረሰኞቹ በበኩላቸው የአቻነት ግብ ፍለጋ የተቃራኒ ቡድን ተከላካይ መስመር የፈተኑ የግብ ማግባት እድሎችን መፍጠር የቻሉ ቢሆንም ኳስ መረብ ማገናኘት ላይ እጅግ ሲቸገሩ ተመልክተናል።

በተለይም አማኑኤል ኤርቦን ኢላማ ያደረጉ በርከት ያሉ ኳሶች ወደ ሶስተኛው ሜዳ ክፍል በፈጣን ሽግግር ሲደርሱ ተስለውሏል። ከፈጠሯቸው አስቆጪ ከሚባሉ አጋጣሚዎች መካከል ፤ 55ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ደግማዊ አርኣያ በግራ መስመር በኩል ኳስ ይዞ በመግባት ያሻማውን ኳስ አማኑኤል ኤርቦ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገው ሙከራ ኢላማውን ሳይጠብቅ የቀረበት 62ኛው ደቂቃ ላይ ፀጋ ከድር ጣጣውን የጨረሰ ኳስ በመስመር በኩል አሻግሮ ብቻውን የነበረው ፉአድ አብደላ ወደ ግብ ቢመታም ፍሬው ጌታሁን በፍጥነት ጨርፎ ያወጣባቸው አጋጣሚ ይጠቀሳል።

ጨዋታው ወደ መገባደጃ ሲቃረብ ፈረሰኞቹ በጫና የአቻነት ግብ ፍለጋ ሙሉ ሀይላቸውን ተጠቀመው የግብ እድል ለመፍጠር ቢጥሩም እጃቸው የገባውን ሶስት ነጥብ ለማስጠበቅ የተከላካይ መስመራቸውን ያጠነከሩትን የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮችን ተከላካይ መስመር አልፈው ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው ጨዋታው በሳይመን ፒተር መጀመሪያ አጋማሽ ብቸኛ ግብ ለሐመራዊ ለባሾች ሶስት ነጥብ በማጎናፀፍ ተቋጭቷል።