ሲዳማ ቡናዎች በደጋፊዎቻቸው ፊት በፍቅረኢየሱስ ተወልደብርሃን ብቸኛ ግብ የጣና ሞገዶችን አሸንፈዋል።
በኢዮብ ሰንደቁ
በ25ተኛ ሳምንት መርሐግብር 9:00 ሲል ሲዳማ ቡናን ከባህርዳር ከተማ ያገናኘ ሲሆን ሲዳማ ቡናዎች ስሑል ሽረን ካሸነፉበት አሰላለፍ ይገዙ ቦጋለን በማሳረፍ በምትኩ ማይክል ኪፕሩቪን ሲያስገቡ በተመሳሳይ ባህርዳር ከተማዎች ኢትዮጵያ ቡናን 2-0 ባሸነፉበት ጨዋታ ይዘውት ከገቡበት አሰላለፍ ሄኖክ ይበልጣልን በማሳረፍ በሞትኩ ግብ አስቆጣሪውን ፍፁም ዓለሙን በማስገባት ጨዋታቸውን ጀምረዋል።
በጨዋታው ጅማሬ ላይ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ተመጣጣኝ የሆነ የኳስ እንቅስቃሴን ያሳየን ሲሆን ወደ ተጋጣሚ ግብ በመድረሱ ረገድ ሲዳማዎች የተሻሉ ነበሩ። 24ኛው ደቂቃ ላይ ሲዳማ ቡናዎች መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ አስቆጥረዋል። ከማዕዘን ምት የተሻገረው እና ጊት ጋትኩት የጨረፈውን ኳስ ያገኘውን ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን ወደ ግብነት ቀይሮ ሲዳማ ቡናን መሪ ማድረግ ችሏል።
ከግቡ መቆጠር በኋላ ባህርዳር ከተማዎች የአቻነት ግብ ለማግኘት በጨዋታ እና በኳስ ቁጥጥር ብልጫ በመውሰድ ግብ ለማግኘት ጥረት ቢያደርጉም ኳሷን ከመረብ ጋር ማዋሃድ ግን ከብዷቸው የነበረ ሲሆን በተቃራኒው ያገኙትን ብልጫ ለማስጠበቅ ሲዳማዎች መከላከልን ምርጫቸው በማድረግ ከሚቋረጡ ኳሶች በመልሶ ማጥቃት ግብ ለማግኘት ሲጫወቱ ተስተውሏል።
የአጋማሹ መጠናቀቂያ ደቂቃ ላይ ሲዳማዎች በፍቅረየሱስ ተ/ብርሀን አማካኝነት ያለቀለት የግብ ሙከራ ማድረግ ቢችሉም በግቡ ቋሚ ወጥቶበታል። ይህንንም ተከትሎ የመጀመሪያው አጋማሽ በሲዳማ ቡና 1-0 መሪነት ተጠናቋል።
ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ያገኘሁትን ብልጫ አስጠብቀው ለመውጣት በሚመስል መልኩ ሲዳማ ቡናዎች መከላከሉ ላይ ትኩረት ሲያደርጉ ባህርዳር ከተማዎች ደግሞ ኳስን መስርተው በመግባት ጎል ለማግኘት ጥረት አድርገዋል። ረዘም ያሉ ደቂቃዎችን ይሄ ነው የሚባል ሙከራ ሳያስመለክተን ቆይቷል።
93ኛው ደቂቃ ላይም ባህርዳር ከተማዎች እጅግ አስቆጪ የሆነ ለግብ የቀረበ ሙከራን ማድረግ ችለው ነበር። መነሻውን ከቀኝ መስመር ያደረገ ኳስ ወንድወሰን በለጠ ከሳጥኑ መስመር ላይ ያቀበለውን ኳስ ተቀይሮ የገባው ሄኖክ ይበልጣል ቢመታውም የሲዳማ ቡና ተከላካዮች ተረባርበው ወደ ውጭ አስወጥተውታል። ባህርዳሮች የመጨረሻውዎችን ደቂቃዎች ይበልጥ ጫና ፈጥረው ማጥቃት ቢችሉም ግን የሲዳማ ቡናን የመከላከል አጥር መናድ ተስኗቸው ጨዋታው በሲዳማ ቡና 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።