ሪፖርት | ሐይቆቹ የውድደር ዓመቱን 5ኛ ድላቸውን አሳክተዋል

ሪፖርት | ሐይቆቹ የውድደር ዓመቱን 5ኛ ድላቸውን አሳክተዋል

በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ ማራኪ ፉክክር በተደረገበት ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ በዓሊ ሱሌይማን ድንቅ ጎል ወላይታ ድቻን 1ለ0 አሸንፏል።


ሀዋሳ ከተማ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ነጥብ ተጋርቶ ከወጣበት ስብስብ እንየው ካሳሁን፣ ዳንኤል አበራ እና አቤኔዘር ዮሐንስን አሳርፈው በረከት ሳሙኤል፣ ብሩክ ታደለ እና ብሩክ ኤልያስ በመያዝ ሲገቡ ወላይታ ድቻዎች በበኩላቸው ከአዳማ ከተማ ጋር ያለጎል ከተጠናቀቀው ጨዋታ ምንም ዓይነት ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ኢንተርናሽናል ዳኛ ሀይለየሱስ ባዘዘው ባስጀመሩት የምሽቱ ጨዋታ በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ ገና ከጅምሩ ነበር በፈጣን እንቅስቃሴ ቶሎ ቶሎ ወደ ጎል መድረስ ጀምሮ የነበረ ቢሆንም የጠሩ የጎል ሙከራዎችን ለማየት ዘለግ ያሉ ደቂቃዎች ወስዷል።

21ኛው ደቂቃ ሀይቆቹ በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ቸርነት አውሽ ኳሱን እየገፋ ሳጥን ውስጥ ገብቶ በተሻለ አቋቋም ለሚገኘው ዓሊ መስጠት ሲችል ራሱ ለመጠቀም አስቦ ሳይጠቀምበት የቀረው እንዲሁም ከሁለት ደቂቃ በኋላ በተመሳሳይ እንቅስቃሴ ዓሊ ሱሌይማን ተከላካይ አልፎ ወደ ውስጥ በመግባት ኳሷን በግብ ጠባቂው ቢንያም ገነቱ እግር ስር ሾልካ መረብ ላይ አረፈች ስትባል ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣችው ሀዋሳዎች በደቂዎዎች ልዮነት የፈጠሯቸው ወርቃማ ዕድሎች ነበሩ።

ጨዋታውን በሚፈልጉት መልኩ እየከወኑ የነበሩት ሀዋሳዎች በየአቅጣጫው ሙከራዎችን ለማድረግ ጥረት ማድረጋቸውን ሲቀጥሉ በወላይታ ድቻ በኩል ጨዋታውን ለመቆጣጠር ተረጋግተው ኳሱን በመያዝ ለመንቀሳቀሰ በሚያደርጉት ሂደት ውስጥ 38ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ቅጣት ምት ሊሰጥባቸው ችሏል።

ማይክል ኦቱሉ ከቀኝ መስመር የተሻገረውን ኳስ ተስፋዬ መላኩ ብሩክ ላይ ያልተመጣጠነ ጉልበት በመጠቀሙ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ዓሊ መቶ ግብጠባቂው ቢንያም ገነቱ በአስደናቂ ቅልጥፍና አድኖ ቡድኑን በጨዋታው ማቆየት ችሏል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ 48ኛው ላይ ሀይቆቹ ያስቆጠሩት ጎል የጨዋታውን ግለት ከፍ አድርጎታል። ከራሳቸው የሜዳ ክፍል በቅጣት ምት የተሻገረውን ኳስ ከሳጥን ውጭ ዓሊ ሱሌማን በአስደናቂ ሁኔታ በግብ ጠባቂው ቢንያም ገነቱ መረብ ላይ አሳርፎት ቡድኑን መሪ አድርጓል።

ካልጠበቁት አቅጣጫ ጎል ያስተናገዱት የጦና ንቦቹ የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን ተጫዋቾች ቀይረው በማስገባት ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለው ከቀኝ መስመር ጠርዝ ላይ ከቅጣት መት በቀጥታ ወደ ጎል የተመታው በሀዋሳ ተከላካዮች ርብርብ ጎል እንዳይሆንባቸው ሆኗል።

ውጤቱን አስጠብቀው መውጣት የፈለጉት ባለ ሜዳዎቹ መከላከልን ምርጫቸው አድርገው ዓሊ ሱሌይማንን ትኩረት ያደረጉ ዕረፍት አልባ የመልሶ ማጥቃት ጥቃቶችን በመሰንዘር አደጋ ለመፍጠር ሞክረዋል። በዚህ ሂደት 74ኛው ደቂቃ ዓሊ ሱሌማን ከራሳቸው የሜዳ ክፍል አንስቶ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ኳሱን እየገፋ በመሄድ የሞከረውን ግብጠባቂው ቢንያም ያዳነበት ለሀዋሳዎች አስቆጪ አጋጣሚ ነበር።

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የጦና ንቦቹ በሙሉ አቅማቸው በጥሩ እንቅስቃሴ ወደ ማጥቃት ቢገቡም አጥቂዎቻቸው በቀላሉ ዕድሎች እንዳይፈጡሩ የሚያባክኗቸው ኳሶች ወደ ጨዋታ እንዳይመለሱ አድርጓቸዋል። በአንፃሩ ሀዋሳዎች ድቻዎች ትተውት የሚሄዱበትን ክፍት ሜዳ ለመጠቀም ጥረት ሲያደርጉ በ88ኛው ደቂቃ ዓሊ ሱሌማን በፍጥነት ከመልካሙ ቦጋለ ጋር ታግሎ አመቻችቶ ቢመታውም ግብ ጠባቂው ቢንያም ያዳነበት ለቡድኑ እፎይታ የሚሰጥ አጋጣሚ ሆኖ አልፏል። ጨዋታው በሀዋሳ ከተማ አንድ ለምንም አሸናፊነት ተጠናቋል።