ቡናማዎቹ እና ዐፄዎቹ የሚያገናኘው የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይገመታል።
ከሰባት ጨዋታዎች በኋላ በባህርዳር ከተማ ከተማ ሽንፈት አስተናግደው ከመሪው ጋር ያላቸው ልዩነት የሚያጠቡበት እና ደረጃቸው የሚያሻሽሉበት ዕድል ያባከኑት ኢትዮጵያ ቡናዎች ዳግም ወደ ድል መንገድ በመመለስ ደረጃቸው ወደ 2ኛነት ከፍ ለማድረግ በጥሩ ብቃት ከሚገኙት ዐፄዎቹ ጋር ይፋለማሉ።
ከሽንፈት በራቁባቸው እና ማግኘት ከሚገባቸው 21 ነጥቦች ውስጥ 17ቱ ካሳኩባቸው ሰባት የጨዋታ ሳምንታት በኋላ በባህርዳር ከተማ ነጥብ ጥለው
ከመሪው ጋር የነበራቸውን የነጥብ ልዩነት የሚያጠቡበት ዕድል ያመከኑት ቡናማዎቹ ምንም እንኳን ከሽንፈት መልስ የሚያደርጉት ጨዋታ ቢሆንም ቀላል ግምት አይሰጣቸውም። ከዚ በፊት በመከላከሉ ረገድ የማያሳማ ብቃት የነበረው ቡድኑ ከተከታታይ ስድስት መርሐ-ግብሮች በኋላ በመጨረሻው ጨዋታ ግብ ከማስተናገዱም በተጨማሪ በዕለቱ የነበረው የመከላከል ውቅር በውስን መልኩ ደካማ ነበር። ለዚህ ቡድኑ በጊዜ ግብ ማስተናገዱ እና የአቻነት ግብ ፍለጋ ለማግኘት በታተረባቸው ደቂቃዎች የኋላ ክፍሉ ይበልጥ ተጋላጭ መሆኑ እንደ ምክንያት መጥቀስ ቢቻልም በጥቅሉ ሲታይ ግን የመከላከል ጥምረቱ በወትሮው ብቃቱ ላይ አልነበረም። በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ስምንት ግቦች ካስቆጠሩት ዐፄዎቹ ጋር በሚደረገው ጨዋታም ወደ ቀድሞ የመከላከል ጥንካሬያቸው መመለስ ይኖርባቸዋል።
ቡናማዎቹ ከተጋጣሚያቸው ባህሪ አንፃር ነገ የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን ለመውሰድ የሚጠብቃቸው ፈተና ቀላል ላይሆን ይችላል፤ በተጋጣሚያቸው የአማካይ ክፍል ጥንካሬ መነሻነትም በርከት ያሉ የጠሩ የግብ ዕድሎች ለመፍጠር መቸገራቸው የሚቀር አይመስልም። ከዚህ በተጨማሪም በሚፈለገው መጠን ግብ እያመረተ የማይገኘውን የፊት መስመራቸው ስልነት መጨመር ነገ የሚጠብቃቸው ስራ ነው።
በሁለተኛው ዙር ጥሩ መሻሻልን እያሳየ የሚገኘው ፋሲል ከነማ መቻል፣ ወልዋሎ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ባሳካቸው ተከታታይ ድሎች ታግዞ በሰንጠረዡ የላይኛው ክፍል ወዳለው ፉክክር መቅረብ ችሏል።
አንድ ነጥብ ብቻ ካሳኩባቸው ሦስት ተከታታይ መርሐ-ግብሮች በኋላ ከወራጅ ቀጠና ስጋት ወደ ሰንጠረዡ ወገብ ያሻገሯቸው አስፈላጊ ድሎች ያስመዘገቡት ዐፄዎቹ በነገውም ጨዋታም ነጥባቸውን ከተጋጣሚያቸው ጋር በማስተካከል እና በሰንጠረዡ ወገብ ለመደላደል እንደሚፋለሙ ይጠበቃል።
ባለፉት ጨዋታዎች ወደ ትክክለኛው ቅርፅ የመጣው ቡድኑ በቅርብ መርሐ-ግብሮች ላይ በማጥቃቱ ረገድ ያሳየው ጉልህ መሻሻል ከእንደ ነገ ዓይነት ተጠባቂ ጨዋታዎች ላይ ሙሉ ነጥብ ይዞ ለመውጣት በሚያስችል ቁመና ላይ እንዳለ አመላካች ነው። በተለይ ደግሞ የቡድኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ እና አምበል በሆነው ጌታነህ ላይ የተገነባ የሚመስለው የቡድኑ የፊት መስመር አስፈሪነቱ እየጨመረ መጥቷል። ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ስምንት ግቦች ያስቆጠረው የማጥቃት ጥምረቱ ጠንካራ የመከላከል ውቅር ጋር ካለው ቡድን የሚጠብቀው ፈተናም ጨዋታው ይበልጥ ተጠባቂ ያደርገዋል።
ጨዋታው በሁለቱ ቡድኖች መሐል ካለው የነጥብ መቀራረብ በተጨማሪ ባለፉት ሳምንታት በጥሩ ብቃት የዘለቁት የማጥቃት እና የመከላከል ጥምረቶች የሚያፋልም እንደመሆኑ ተጠባቂ ነው።
በኢትዮጵያ ቡና በኩል ሁሉም የቡድን አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው። በፋሲል ከነማ በኩል ብሩክ አማኑኤል እና ማርቲን ኪዛ በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጪ ሲሆኑ የኢዮብ ማቲያስ መሰለፍም አጠራጣሪ ነው። ከዛ ውጪ ግን ሁሉም የቡድኑ አባላት ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው።
ሁለቱ ክለቦች በሊጉ እስካሁን 16 ጊዜ የእርስ በእርስ ጨዋታዎች ያደረጉ ሲሆን ፋሲል ከነማ 5 ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ 4 ድሎችን ሲያሳኩ ቀሪዎቹ ሰባት ጨዋታዎች ነጥብ በመጋራት ተጠናቀዋል። ፋሲል ከነማዎች በእነዚህ ጨዋታዎች 15 ግቦችን ሲያስቆጥሩ ኢትዮጵያ ቡናዎች ደግሞ 14 ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል። (የተሰረዘው የ2012 የውድድር ዓመት አልተካተተም)