በቀደመ የግንኙነት ታሪካቸው እኩል የድል እና የግብ መጠን ማስመዝገብ የቻሉት መቻል እና አርባምንጭ ከተማ ከፍ ያለ የደረጃ መሻሻል የሚያስገኝላቸውን ድል ለማግኘት ይፋለማሉ።
ዓመቱን በጀመሩበት ፍጥነት መዝለቅ ያልቻሉት መቻሎች እጅግ ወሳኝ በነበረው የመጨረሻው ጨዋታ መቐለ 70 እንደርታ ላይ የተቀዳጁት ድል በማስቀጠል ደረጃቸውን ለማሻሻል ወደ ሜዳ ይገባሉ።
9ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ቡድኑ ከነገው ተጋጣሚው በሁለት ነጥቦች ዝቅ ብሎ ሰላሣ ሁለት ነጥቦች ሰብስቧል፤ ጦሩ የነገው ጨዋታ በድል የሚወጣ ከሆነ ከአስራ ሁለት የጨዋታ ሳምንታት ጥበቃ በኋላ በሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ሙሉ ነጥብ ከማግኘቱም በላይ በደረጃ ሰንጠረዡ ብያንስ ሦስት ደረጃዎች የመሻሻል ዕድል በእጁ ይገኛል። መቻሎች በመጨረሻው ጨዋታ ካሰመዘገቡት ድል በተጨማሪ ጨዋታውን በመቆጣጠር ረገድም ጥሩ አፈፃፀም አሳይተዋል፤ ሆኖም በርከት ባሉ ጨዋታዎች በመገባደጃ ደቂቃዎች በተጋጣሚ የሚፈጠርባቸው ጫና በመቀነስ በኩል ተጨማሪ ስራዎች መስራት ይጠበቅባቸዋል። አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ከድሉ በኋላ እንዳነሱት የቡድኑ የአሸናፊነት መንፈስ ከፍ ማድረግም ሌላው የሚጠብቃቸው ስራ ነው።
ቡድኑ ጥሩ በተንቀሳቀሰባቸው እና የግብ ዕድሎች በፈጠረባቸው ጨዋታዎች ላይ በሚፈለገው መጠን ግብ ማስቆጠር አለመቻሉም ከሁሉም በላይ አሰልጣኙን የሚያሳስባቸው ጉዳይ ነው፤ በነገው ዕለትም ድል አድርጎ ለመውጣትም ከፍ ባለ የማሸነፍ ስነ ልቡና ራሳቸውን በአዕምሮው ረገድ በማዘጋጀት በግብ ፊት ያለባቸው የአፈፃፀም ድክመት መቅረፍ ይጠበቅባቸዋል።
ባልተጠበቀ መልኩ በመቐለ 70 እንደርታ ከተረቱበት ጨዋታ በኋላ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስቴድየም በተካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች በእኩሌታ ድል እና የአቻ ውጤት ያስመዘገቡት አዞዎቹ ነጥብ ከተጋሩበትና ፈታኝ ከነበረው የመጨረሻው ሳምንት ጨዋታ መልስ ሙሉ ነጥብ ለማስመዝገብ ጦሩን ይገጥማሉ።
አዞዎቹ በሰላሣ አራት ነጥቦች 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። በሁለተኛው ዙር ማግኘት ከሚገባው አስራ አምስት ነጥቦች አስሩን ማሳካት የቻለው ቡድኑ በነገው ተጠባቂ ጨዋታ ድል ማድረግ ከቻለም በ2ኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው ባህርዳር ከተማ በነጥብ ተስተካክሎ የዋንጫ ፉክክሩን የሚቀላቀልበት ወርቃማ ዕድል አለው። ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ሰባት ግቦች ማስቆጠር የቻሉት አርባምንጮች ዋነኛው ጠንካራ ጎናቸው የሆነው የፊት መስመር ጥንካሬ ማስቀጠል መቻላቸው በአወንታዊ ጎኑ የሚነሳላቸው ነጥብ ነው፤ በተጨማሪም ከዚህ ቀደም በአሕመድ ሔሴን ጫንቃ ብቻ የነበረው የግብ ማስቆጠር ኃላፊነት በአዲሱ ፈራሚ ታምራት እያሱ እና አንዱዓለም አስናቀ መታገዝ መጀመሩ ቡድኑን ይበልጥ አጎልብቶታል።
ለቡድኑ ትልቅ የደረጃ መሻሻል በሚያስገኘው የነገው ጨዋታም የማጥቃት ጥንካሬውን ከማስቀጠል ባለፈ ከመቻል የአማካይ ክፍል ለሚጠብቃቸው ፈተናም መዘጋጀት ይኖርባቸዋል።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለ19 ጊዜያት ያህል የተገናኙ ሲሆን ሁለቱም በእኩሌታ 6 ጨዋታዎች ድል ስያደርጉ በቀሪዎቹ 7 ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርተዋል። አዞዎቹ 16 መቻሎችም በተመሳሳይ 16 ጎሎችን በግንኙነታቸው አስቆጥረዋል።
በመቻል በኩል ጉዳት የሰነበተው በረከት ደስታን ጨምሮ ሁሉም የቡድኑ አባላት ለነገው ጨዋታ ዝግጁ መሆናቸው ተመላክቷል። በአርባምንጭ ከተማ በኩል ያለውን የቡድን ዜና ለማግኘች ያደረግነው ጥረት ግን አልተሳካም።