ሪፖርት | ቡናማዎቹ ለመጀመርያ ጊዜ በአንድ የውድድር ዓመት ዐፄዎቹን ሁለት ጊዜ አሸንፈዋል

ሪፖርት | ቡናማዎቹ ለመጀመርያ ጊዜ በአንድ የውድድር ዓመት ዐፄዎቹን ሁለት ጊዜ አሸንፈዋል

በተጠባቂው ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና በኮንኮኒ ሀፊዝ ብቸኛ ጎል ፋሲል ከነማን 1ለ0 በመርታት ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከፍ ብሏል።

በቡናማዎቹ ባሳለፍነው ሳምንት በባህር ዳር ከተማ  ከተረቱበት አሰላለፍ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል። ወልደአማኑኤል ጌቱ እና አማኑኤል አድማሱ በዋሳዋ ጄኦፍሪ እና ስንታየሁ ዋለጬ ተክተው ሲገቡ ዐፄዎቹ በተመሳሳይ ቅዱስ ጊዮርጊስን ድል ካደረገው ስብስባቸው የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል። ሸምሰዲን መሀመድ እና አንዋር ሙራድ አርፈው በእዮብ ማትያስ እና ቢንያም ላንቃሞ በመያዝ ወደ ሜዳ ገብተዋል።

የሳምንቱን ተጠባቂ ጨዋታን ኢንተርናሽናል ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ ሲያስጀምሩት በስታዲየሙም ዝናብ እየዘነበ ነበር። ተመጣጣኝ ፉክክር በታየባቸው የመጀመሪያ 20 ደቂቃዎች ያን ያህል ተጠቃሽ ሙከራ ባይደግበትም በሁለቱም በኩል በቁጥር በዝተው የጎል አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ጥረቶች ነበሩ። 21ኛው ደቂቃም የጨዋታው የተሻለ የመጀመሪያ ሙከራም በጌታነህ ከበደ ጠንካራ ምት ግብ ጠባቂው ዳላንድ ኢብራሂም ይዞበታል። ብዙም ሳይቆይ ከሦስት ደቂቃ በኋላ ቡናማዎቹ በመጀመርያ ሙከራቸው የመጀመርያ ጎላቸውን ማግኘት ችለዋል። ከቀኝ መስመር ወደ ፊት የመጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች ዲቫይን የሰጠውን ስንታየሁ ወደ ጎል ሲመታው በተከላካዮች ሲደረብ እግሩ የገባችውን ኳስ ኮንኮኒ ሀፊዝ በጥሩ አጨራረስ አስቆጥሮታል።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ የአቻነት ጎል የፈለጉት ዐፄዎቹ በእንቅስቃሴ ደረጃ ተደረጅተው ከራሳቸው የግብ ክልል ለመውጣት ቢችሉም ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ደርሰው የጠሩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር  ከመቸገራቸውም ባሻገር የቡናማዎችን የመከላከል አጥር ጥሰው ለመግባት ተቸግረዋል።  በአንፃሩ ኢትዮጵያ ቡና  በ33ኛው ደቂቃ ቀዳሚውን ጎል ያስቆጠረው ኮንኮኒ ሀፊዝ ከፈጠረው የጎል አጋጣሚ ውጭ ተጨማሪ ዕድሎችን ባይፈጥሩም እግራቸው ኳሱ ሲገባ በሚያገኙት ክፍት ሜዳ ወደ ፊት በመሄድ ጫና ለማሳደር ጥረት ሲያደርጉ አስተውለናል። አጋማሹም በቡናማዎቹ 1-0 መሪነት ተጠናቋል።

በዝናብ ታጅቦ ሁለተኛው አጋማሽ ጅማሬውን ሲያደርግ አቤል እንዳለ እና አማኑኤል ገብረሚካኤልን ቀይረው ያስገቡት ዐፄዎቹ ወደ ጨዋታው ለመመለስ የሚችሉበትን ወርቃማ ዕድል 51ኛው ደቂቃ ላይ መፍጠር ችለው ነበር። በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ከግራ መስመር ከጀርባ የመጣው ኪሩቤል በጥሩ መንገድ ወደ ውስጥ የላከውን ጌታነህ ከበደ ግብ ጠባቂውን ዳላንድ አልፎ ኳስና መረብን አገናኘ ሲባል ኳሷን ወደ ሰማይ የሰደዳት ለፋሲሎች የምታስቆጭ አጋጣሚ ነበረች።

ወደ ራሳቸው የግብ ክልል በመጠጋት ጨዋታውን ማረጋጋት የፈለጉት ቡናማዎቹ በመልሶ ማጥቃት አደጋ ይፈጥሩ ነበር። በዚህ ሂደት 69ኛው ደቂቃ አንተነህ ተፈራ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን ቅጣት ምት ዲቫይን በጥሩ መንገድ  የመታውን ግብ ጠባቂው ፋሲል ወደ ውጭ አውጥቶበታል። ከሦስት ደቂቃ በኋላም ቡናማዎቹ ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኮንኮኒ ሀፊዝ በመቅስ ምት የመታው ኳስ ለጥቂት ወደ ውጭ ወጥቶበታል ።

ጨዋታው ከፍ ወደ አለ ፉክክር አምርቶ በ75ኛ ደቂቃ ከግራ መስመር ጠርዝ ጌታነህ ከበደ የመታውን ቅጣት ምት ግብ ጠባቂው ዳላንድ ወደ ውጭ ካወጣበት በኋላ 84ኛው ደቂቃ ዐፄዎቹ በፈጣን  የማጥቃት ሽግግር ከምኞት የተላከውን አማኑኤል ገብረሚካኤል ኳሱን ለማግኘት በሚያደርገው ሩጫ የቡናማዎቹ ተከላካይ ረጀብ ሚፊታህ አማኑኤልን ሚዛኑን አስተሀል በሚል በሁለት ቢጫ ማስጠንቀቂያ በቀይ ካርድ ከሜዳ እንዲወጣ ተደርጓል።

በቀሩት ደቂቃዎች የቁጥር ብልጫውን ተጠቅመው ፋሲሎች በተሻለ የኳስ ቁጥጥር ወደፊት ተጭነው ለመጫወት ጥረት ቢያደርጉም ቡናማዎቹ በተረጋጋ አጨዋወት ውጤቱን አስጠብቀው ወጥተዋል። ጨዋታውም  በኢትዮጵያ ቡና 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።