የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር የሆኑት አብርሃም መብራቱ ከሴቶች ልማት ጋር ተያይዞ በሰጡት ሙያዊ አበርክቶ ከካፍ የእውቅና ደብዳቤ ተሰጥቷቸዋል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው በጣት የሚቆጠሩ የካፍ ኢንስትራክተሮች መካከል ኤሊት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ አንዱ ናቸው። ከ2007 ጀምሮ በቀጠናዊ ኢንስትራክተርነት፣ ከ2014 ጀምሮ በአህጉራዊ ኢንስትራክተርነት፣ ከ2018 ጀምሮ ደግሞ በኤሊት ኢንስትራክተርነት እንዲሁም ከ2022 ጀምሮ በፊፋ ቴክኒካል ኤክስፐርትነት ሀገራቸውን እንዲሁም አህጉራቸውን እያገለገሉ የሚገኙት የቀድሞ የየመን እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ በአሁኑ ሰዓት ከሚሰሩት የመቻል ስፖርት ክለብ ቴክኒክ ዳይሬክተርነት ሚና ጎን ለጎን አሠልጣኞችን ለማብቃት በተለያዩ ሀገራት ስልጠናዎችን እየሰጡ እንደሚገኝ ይታወቃል።
ያለፉትን ቀናት ከሴቶች እግርኳስ ጋር በተገናኘ በተለያዩ ሀገራት ለሚገኙ ኢንስትራክተሮች ከልምምድ መርሐ-ግብር እቅድ እና የአሠልጣኝነት ሂደት እንዲሁም ከኢንስትራክተሮች ሚና ጋር በተገናኘ ስልጠና ሲሰጡ የነበሩት አብርሃም መብራቱ በስልጠናው ሂደት ልምዳቸውን በማጋራታቸው እና በሰጡት ትምህርት ካፍ የምስጋና እና የዕውቅና ደብዳቤ እንደላከላቸው የዝግጅት ክፍላችን አውቃለች።
